“የዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ተግባር ዲጅታላይዝ በኾነ አሠራር ይከናወናል” ግብርና ቢሮ

6

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት የአረንጓዴ ልማት ተግባራት ላይ ምክክር እያደረገ ነው፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ መሰሉ ብርሃኑ ክልሉ ከአረንጓዴ አሻራ አኳያ በስምንት ዓመት ውስጥ ብዙ ለውጦች የመጡበት ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል። በዚህም የወጣቶች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ነው የገለጹት።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማጠቃለያ በኾነው በዚህ ዓመት 1 ነጥብ 78 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ እንደተያዘ ነው የገለጹት። ለዚህም 97 በመቶ የሚኮን የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል። ቀሪ ጥቂት ሥራዎች በተያዘው ሳምንት ይጠናቀቃሉ ነው ያሉት። በተያዘው ዓመትም የአማራ ወጣቶች ፎረም ተሳትፎ እና ተነሳሽነት ላቅ ያለ እንዲኾን ይጠበቃል ነው ያሉት።

የዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ተግባር ዲጅታላይዝ የኾነ አሠራርን የሚከተል ኹኖ የሚተገበር በመኾኑ ከቀደሙ ዓመቶች ልዩ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት። በአንድ ቀን ጀምበር የሚከናወኑ የችግኝ ተከላ ሥራዎቻችን የማስጀመሪያ መርሐግብር በፌዴራል ደረጃ ሰኔ 22/2018 ዓ.ም በአማራ ክልል ደግሞ ሰኔ 25/2018 ዓ.ም እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

ሐምሌ አጋማሽ ላይ በሚከናወነው የአንድ ቀን ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐግብር 318 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በችግኝ ይሸፈናል ብለዋል። ለዚህም ክልሉ ውስጥ ባሉ ሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ወጣቶች ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

የአማራ ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም ፕሬዝዳንት በለጠ ወዳጅነው ፎረሙ ከተመሠረተባቸው መሠረታዊ መርሆች አንዱ አረንጓዴ ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደኾነ ተናግረዋል። በአየር ንብረት ጉዳይ ላይም አጀንዳዎችን ያቀነቅናል፤ ግንዛቤ ይፈጥራል፣ ባለድርሻ አካላትን ያስተባብራል ነው ያሉት። ፎረሙ አረንጓዴ አሻራ ከተጀመረ ጀምሮ በክረምት ወራት በንቅናቄ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በየዞኑ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን በበጋ ወቅት በመንከባከብም ትልቅ ሥራ ሠርቷል ብለዋል። ይህም በክልሉ ብቻ ሳይኾን ከክልሉ ውጭ በመንቀሳቀስ የሌላ ክልል ወጣቶችን በማስተባበር ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። በዚህ ዓመትም ከእስካሁኑ በተለየ ከሌሎች አካባቢ ወጣቶች ጋር የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ እንፈጥራለን፤ ለዚህም ልዩ ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ወጣቶች አረንጓዴ ፎረም አባል ወጣት ቴወድሮስ አደራጀው ደግሞ የአረንጓዴ ፎረም ንቅናቄ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወጣቱ በበጎ ፈቃደኝነት ወደ ተራቆቱ ቦታዎች እየተንቀሳቀሰ ችግኞች በመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከመታወጁ አስቀድሞ በአማራ ክልል በንቅናቄ ሲሳተፍ መቆየቱን ተናግሯል።

#አሚኮ_ዜና #አረንጓዴ_አሻራ_አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥናት እና ምርምር የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ሳይንሳዊ መሠረት ተደርጎ መታየት አለበት” አቶ ዓለምአንተ አግደው
Next article“አሚኮ የጸጥታ ችግር ሳይበግረው ሕዝብ እና መንግሥትን በድልድይነት እያገናኘ ያለ የአማራ ክልል ምልክት ነው” አቶ አበራ ፋንታሁን