
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት ዓመታዊ የጥናት እና ምርምር ጉባዔን እያካሄደ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ጉባዔው የክልሉ የፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት በክልሉ ምክር ቤት ሙያዊ ነጻነቱን ጠብቆ እንደገና ከተደራጀ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ የጥናት እና ምርምር ጉባዔ መኾኑን ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ በአዲሱ አዋጅ ከተሰጠው ተልዕኮ መካከል የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት አሠራር ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ገለልተኛ እና የሕዝብ አመኔታን ያተረፈ ለማድረግ የሚያግዙ ሳይንሳዊ ጥናት እና ምርምሮችን ማካሄድ አንደኛው መኾኑን ተናግረዋል። በዚህ መሠረትም ጥናት እና ምርምሮችን ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።
ካካሄዳቸው ጥናት እና ምርምሮች መካከልም በክልሉ እውነተኛ መረጃ ላይ የተመሠረቱ እና በይዘት ትንተና የተዘጋጁ አራት ጉዳዮች በጉባዔው ለውይይት መቅረባቸውን ተናግረዋል።
እነዚህም፦
👉 በመንግሥት ጉዳዮች የፍትሐ ብሔር ክርክር የፍርድ አፈጻጸም በአማራ ክልል ሕግ እና አተገባበሩ፤
👉የንቃተ-ሕግ ትምህርት አሰጣጥ ሒደት እና ውጤታማነት፤
👉 የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ አፈጻጸም ውጤታማነት እና በሴቶች ላይ በሚፈጸሙ ወሲባዊ ወንጀሎች የፖሊስ ወንጀል ምርመራ የዳሰሳ ጥናት በአማራ ክልል የሚሉ እንደኾኑ ዘርዝረዋል።
ጥናት እና ምርምሮቹ የሕግ ክፍተቶችን ከመለየት ባለፈ መዛግብትን እና የባለሙያዎችን የሥራ ተሞክሮ ያጣመሩ እና ክፍተቶችን በግልጽ የሚያሳዩ ናቸውም ብለዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የኢንስቲትዩቱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዓለምአንተ አግደው ኢንስቲትዩቱ እንደገና ከተደራጀ በኋላ ሰፋፊ የለውጥ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል።
የጥናት እና ምርምር ጉዳዮችን ከመለየት ጀምሮ ሂደቱ ሳይንሳዊ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲሠራ የሚያስችል የአሠራር ማጠናከሪያ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እንደሠራም ነው ያነሱት።
የዳኝነት ነጻነት፣ የሕግ የበላይነት እና የተቋማት ገለልተኛነት በፖለቲካዊ ፍላጎት ወይም በተቋማት መመሪያዎች ብቻ እንደማይገነቡ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ይልቁንስ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ በሚመሠረት ሳይንሳዊ እና መዋቅራዊ ለውጥ የሚረጋገጡ ናቸው ብለዋል።
ጥናት እና ምርምር እንደ አንድ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ሳይንሳዊ መሠረት ተደርጎ መታየት አለበት ነው ያሉት።
ጥናትና ምርምር በፍትሕ ሥርዓቱ ያለው ሚና የአሠራር ክፍተቶችን መዘገብ ብቻ አይደለም ብለዋል። ይልቁንም የተቋማትን ነባራዊ ቁመና በጥልቀት በመመርመር ሕጋዊ እና መዋቅራዊ መፍትሔዎችን ለመጠቆም ያግዛል ነው ያሉት። በግምት እና በተለምዶ ላይ የሚመሠረቱ ፖሊሲዎች የሕዝብ አመኔታን እና እርካታን ማረጋገጥ እንደማይችሉም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
