
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባስተላለፈው ወቅታዊ መልእክት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ዳር ድንበር ከመጠበቅ እና የውስጥ ሰላምን ከማስከበር ባለፈ በምሥራቅ አፍሪካ አስተማማኝ መረጋጋት እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ የሚገኝ የሰላም ግንባታ ምሰሶ መኾኑን ገልጿል።
ሠራዊቱ የብሔር፣ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ወገንተኝነት ሳይኖረው የሁሉንም ኢትዮጵያውያን እሴት በመወከል ከውስጥ እና ከውጭ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት የሀገርን ህልውና እያስከበረም ይገኛል ነው ያለው ቢሮው በመልእክቱ።
ከተለመደው ወታደራዊ ግዳጅ ባሻገር በበጋ እና በክረምት በመስኖ ልማት፣ በሰብል ሥብሠባ፣ በችግኝ ተከላ እንዲሁም በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ወቅት ከሕዝብ ጎን በመሰለፍ የሀገርን ልማት እያፋጠነ ስለመኾኑም አስረድቷል።
እንደ አልሸባብ ያሉ አሸባሪ ቡድኖችን በመመከት ረገድ ግንባር ቀደም ተዋናይ ከመኾኑም በላይ በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በአብዬ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በስኬት በመወጣት የብዙዎችን ሕይወት ስለመታደጉም ነው የተጠቆመው።
ሠራዊቱ ወቅታዊውን የቴክኖሎጂ እና የጂኦፖለቲካዊ ለውጦች ከግምት ውስጥ በማስገባት የአየር ኀይል፣ የባሕር ኀይል እና የሳይበር ደኅንነት መዋቅሮቹን በዕውቀት፣ በሥልጠና እና በዘመናዊ ትጥቅ እያደራጀ ይገኛልም ብሏል።
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መልእክቱን ሲያጠቃልልም ይህንን የሀገር ኩራት የኾነ ሠራዊት በሀሳብ፣ በሞራል እና በሁሉም መስክ መደገፍ የእያንዳንዱ ዜጋ ታሪካዊ ኀላፊነት መኾኑንም አሳስቧል።
#አሚኮ_ዜና #መከላከያ_ሠራዊት_ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
