የደብረ ማርቆስ – ባሕር ዳር አስፋልት መንገድ ዳግም ግንባታ ዲዛይን ተጠናቋል።

6

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ አበባን በደብረ ማርቆስ በኩል ከባሕር ዳር የሚያገናኘው የአስፋልት መንገድ አንድ መስመር ብቻ መኾኑ፣ ስፋቱም በሚፈለገው ልክ ባለመኾኑ ነዋሪዎች እና የከተማ አሥተዳደሮች ተደጋጋሚ ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።

የፍኖተ ሰላም ከተማም በከተማዋ መሀል የሚያልፈው መንገድ እና ድልድይ በረጅም ዘመን የአገልግሎት ጊዜው ለጉዳት መዳረጉን የፍኖተ ሰላም ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጊዜው ደግአረገ ጠቁመዋል። ይህም በከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እና የአደጋ ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት።

መንገዱ ለሀገር አቀፍ ኢኮኖሚ፣ ለሕዳሴው ግድብ እና ለቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ነው። መንገዱ እየደረሰበት ባለው ከፍተኛ ጫና ምክንያት የመዘጋት አደጋ ካጋጠመው አማራጭ መውጫ የሌለው በመኾኑ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ችግሩን ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ማሳወቅ መቻሉንም አስታውሰዋል። ኅብረተሰቡም ለመንገዱ ግንባታ ሲባል በ30 ሜትር የወሰን ክልል ውስጥ የነበሩ ቦታዎችን አፍርሶ መንገዱን ክፍት አድርጓል።

ከሕዝቡ ጋር በመተባበርም የውስጥ ለውስጥ የመንገድ እና የ900 ሜትር የአስፋልት ኮሪደር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በዘንድሮው ዓመት በጨረታ ሂደት ላይ መኾኑ ከመንገዶች አሥተዳደር በኩል ቢገለጽም እስካሁን ወደ ተግባራዊ ግንባታ እንዳልተገባ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የተጓተተውን የዋናው አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በፍጥነት እንዲያስጀምርም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የደብረማርቆስ መንገድ አውታር አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ደርበው ድልነሳ የትራፊክ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ የደብረ ማርቆስ – ባሕር ዳር መንገድ ዳግም ግንባታ ዲዛይን ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን አስታውቀዋል። ሥራውም በሦሥት ሎት ተከፍሎ ይከናወናል።

በአሁኑ ወቅት ከደብረ ማርቆስ – ፍኖተ ሰላም የሎት አንድ መንገድ ፕሮጀክት በጨረታ ሂደት ላይ መኾኑን ጠቁመዋል።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አስቀድሞ መንገድ እንዲሰፋለት መጠየቁንም አስታውሰዋል። የመንገዶች አሥተዳደር ሥራውንም የሚያከናውነው በተቋራጭ መኾኑን ጠቁመዋል። ኾኖም ከተሞች በዲዛይኑ መሠረት በራሳቸው አቅም መሥራት ከቻሉ ተቋሙ የቴክኒክ ድጋፍ እና ዲዛይን እንደሚሰጥ ተናግረዋል። የእንጅባራ ከተማ ተሞክሮንም በአርዓያነት አንስተዋል።

ከተሞች አላስፈላጊ ወጭን ለማስቀረት አስቀድመው ከመንገድ ባለሥልጣኑ ጋር በቅንጅት መሥራት እና ኮንትራክተሩ ሥራ ሲጀምር የይዞታ ችግር እንዳያጋጥም ቦታዎችን ነጻ አድርጎ መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በከተማዋ ማረሚያ ቤት አካባቢ የሚገኘው ድልድይ የነበረበት ስንጥቅ ተጠግኖ አሁን ላይ በቴክኒክ ደረጃ ምንም ስጋት የለም ብለዋል። በቀጣይም በድልድዩ ላይ የሚታየውን የውኃ መቆም ችግር ለማስተካከል ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት።

በሆስፒታሉ አጠገብ የሚገኘው ሁለተኛው አሮጌ ድልድይ በማንኛውም ሰዓት ሊናድ የሚችል እና ከፍተኛ አደጋ የተደቀነበት በመኾኑ ተለዋጭ መንገዱን መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።

#አሚኮ_ዜና #የመንገድ_ልማት_ፍኖተሰላም_አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እውነት ከቤት ሳትወጣ ውሸት ዓለምን የምታዳርስበት ጊዜ ላይ ነን”
Next articleመከላከያ ሠራዊት አስተማማኝ መረጋጋት እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል።