
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሀሰተኛ መረጃ በሕዝቦች ዘንድ የሚያስከትለው ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ እየኾነ ነው። መነሻ ዓላማዊ ለበጎ ቢኾንም አኹን ግን ለዓለም ሕዝቦች ፈተናነቱ በርትቷል።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መመህር እና ተመራማሪው አበራ የኔወርቅ (ዶ.ር) ማኅበራዊ ሚዲያ ስሪቱ ማኅበረሰብን ማገናኘት፤ ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማጋራት፤ ማስተዋወቅ እና ሌሎች ተያያዥ በጎ ዓላማዎች ያሉት ነው ይላሉ።
ነገር ግን የአጠቃቀም ውስንነት ዓላማውን እንዳሳተው ገልጸዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ለረጅም ዓመታት አብረው ይኖሩ የነበሩ እና የተለያዩ ጉዳዮችን ሲጋሩ የነበሩ ማኅበረሰቦች ትስስር ላይ ጥርጣሬ እየፈጠረ መኾኑን ጠቁመዋል።
ሀሰተኛ መረጃዎች ከእውነተኛ መረጃዎች በላቀ 70 በመቶ የመዛመት ዕድል እንዳላቸውም ጥናቶች ያሳያሉ” ነው ያሉት መምህሩ። መረጃን ከማጋራት በፊት ቢያንስ ለ10 ሴኮንድ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ማስረጃ መኖሩን፣ በስሜት የወጣ አለመኾኑን፤ ኀለፊነት የሚወስዱ ሚዲያዎች መዘገባቸውን፤ መረጃው የተሠራበትን ጊዜ ማረጋገጥ እና የመረጃ አጋሪ አካል ስላስተላለፈው መረጃ ያለውን ዕውቀት በዝርዝር መፈተሽ ይገባልም ብለዋል።
አሁን ላይ እውነት ከቤት ሳይወጣ ውሸት ዓለምን እንደሚያዳርስ የተናገሩት መምህር እና ተመራማሪው ሀሰተኛ መረጃ ዘላቂ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መረጃ ማጣራት ላይ እንደ ሀገር የሚሠሩ መገናኛ ብዙሃን ቁጥር ጥቂት የሚባሉ እንደኾነም አንስተዋል። ቢያንስ በየክልሉ አንድ የመረጃ አጣሪ ተቋም ማደራጀት እንደሚያስፈልግም መክረዋል።
በሕገ መንግሥቱ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 መሠረት ሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ማሠራጨት ከሁለት እስከ አምስት ዓመት እንደሚያስቀጣ ተቀምጧል ብለዋል።
ይህን የተላለፉ ሚዲያዎች ላይ ግን እርምጃ የመውሰድ ውስንነት አለ ነው ያሉት።
ሌሎች ሀገራት የወጣቶች የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዘመቻ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ላይም የሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ላይ ዘመቻ ተካሂዶ ግንዛቤ መፈጠር እንዳለበት ነው የተናገሩት።
ማኅበረሰቡ ከሀሰተኛ መረጃ እፎይታ የሚያገኝበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
