በሚገባው ልክ ጥቅም ላይ ለማዋል ሰላምን የሚሻው የዕጣን እና ሙጫ ምርት ፤

7

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ካለው 760 ሺህ ሄክታር በላይ የደን ሀብት ውስጥ 230 ሺህ ሄክታር የሚኾነው መሬት በዕጣን እና ሙጫ ዛፍ የተሸፈነ ነው። ይህ የተፈጥሮ ስጦታ በሽዎች ለሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የኑሮ መሠረት በመኾን እያገለገለ ይገኛል።

ይሁን እንጂ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ስጋት ለበርካታ የእጣን እና ሙጫ አምራቾች እንቅፋት ኾኖባቸዋል።

በመተማ ወረዳ የለምለም ተራራ እጣን እና ሙጫ አምራች ማኅበር ሊቀመንበር የኾኑት አቶ ሙሐመድ አደም ባለፉት ዓመታት ደኑን እንደ ዐይን ብሌን እየጠበቁ በየዓመቱ ከፍተኛ ገቢያ ያገኙ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ዘንድሮ ማኅበራቸው 200 ኩንታል ለማምረት አቅዶ የነበረ ቢኾንም በአካባቢው በተፈጠረው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ያሰቡትን ያህል ማምረት እንዳልቻሉ ለአሚኮ ገልጸዋል።

በመተማ እና ቋራ ወረዳዎች የእጣን እና ሙጫ ምርት በብዛት በማምረት ላይ የሚገኙት ባለሃብት እና የአልፋሽቃ ትሬዲንግ ድርጅት ወኪል አቶ አፈራ መንግሥቱም በበጀት ዓመቱ 2ሺህ 500 ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ አልመው ወደ ሥራ ገብተው ነበር።

በአካባቢው ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ግን የባለሙያ እጥረት እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ባገኙት የሠው ኀይል እስካሁን 700 ኩንታል የሚኾን የዕጣን እና ሙጫ ምርት መሰብሰብ መቻላቸውን ነው የገለጹት።

አሁን ላይ ምርታቸውን ወደ ማዕከላዊ ገበያ እያቀረቡ መኾኑን የገለጹት አቶ አፈራ አንድ ኩንታል እጣን ከ100 ሺህ እስከ 105 ሺህ ብር እየተሸጠ መኾኑንም ጠቁመዋል።

የራሳቸውን ምርት ጨምሮ የሌሎች ማኅበራትን ምርት በመግዛት ወደ ውጭ ኤክስፖርት እያደረጉ መኾኑንም ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የደን ባለሙያ መኳንንት ደረበ እንደሚሉት በ2018 ዓ.ም የምርት ዘመን 11 ሺህ ኩንታል የእጣን እና ሙጫ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ ነበር። ኾኖም እንደ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት እስካሁን መሠብሠብ የተቻለው 5 ሺህ 625 ኩንታል ብቻ ነው።

በጸጥታ ስጋትም ኾኖ የተገኘው ምርት ግን በማዕከላዊ ገቢያ በተሻለ ዋጋ እየተሸጠ ነው ብለዋል።

እስካሁን ማዕከላዊ ገበያ ከገባው “ነጭ እጣን” ላይ ብቻ ለመንግሥት ከ14 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ የሮያሊቲ ገቢ ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት ባለሙያው።

የምዕራብ ጎንደር ዞን የዕጣን እና ሙጫ ሃብት የወጣቶች የኑሮ ምሰሶ እና የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ይሁን እንጅ ይህን የተፈጥሮ በረከት ለሀገር እንዲተርፍ ከተፈለገ በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እና ጸጥታ መከበሩ ለነገ የማይባል ወሳኝ ጉዳይ እንደኾነም ነው ባለሙያው ያስረዱት። ለዚህም ማኅበረሰቡ ትልቅ ኀላፊነት ወስዶ ከዞኑ አሥተዳደር ጋር እንዲሠራ ነው ያሳሰቡት።

#አሚኮ_ዜና #እጣን_ሙጫ_አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ

ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከተሳሳተ የትጥቅ ትግል ወደ ልማት አርበኝነት !
Next article“እውነት ከቤት ሳትወጣ ውሸት ዓለምን የምታዳርስበት ጊዜ ላይ ነን”