
ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሥራ ባሕልን ያነጹ፣ ለሌሎች የሥራ ዕድልን የፈጠሩ፣ ከጥፋት እና ሱሰኝነት የራቁ፣ ለሌሎች ወጣቶች አርዓያ መኾን የቻሉ በርካታ ወጣቶች አሉ።
በአንጻሩ ደግሞ በሀሳብ ውዥንብር ተጠልፈው የጥፋት ኃይል እንቅስቃሴን ተቀላቅለው የነበሩ ነገር ግን መንገዳቸው የተሳሳተ መኾኑን የተረዱ ወጣቶች አሁን ላይ ከጥፋት መንገድ ወጥተው በልማት ሥራ ላይ የተሠማሩም አሉ።
ወጣት ደጀን ጫቅሉ በተሳሳተ እሳቤ የትጥቅ ትግልን ተቀላቅሎ መቆየቱን ለአሚኮ ተናግሯል። ኾኖም የጥፋት ኃይሉ እንቅስቃሴ በሕዝብ ላይ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና በማሳደሩ የሰላምን አማራጭ መቀበሉን ገልጿል።
በተሃድሶ ኮሚሽን ሥልጠና በመውሰድ በመንግሥት የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ አሁን ላይ 🐂 በእንስሳት ድልብ ሥራ ላይ ተሠማርቶ ይገኛል።
መንግሥት በማኅበር በማደራጀት የሥራ ቦታ የሰጣቸው ሲኾን 15 እንስሳትን እያደለበ ነው።
ያለ ሰላም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና የሀገር ሉዓላዊነት አይረጋገጥም ያለው ወጣት ደጀን በጥፋት እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል ከጽንፈኝነት ወደ ልማት አርበኝነት እንዲመለሱም መልዕክት አስተላልፏል።
በአማራ ክልል ግጭት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ33 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ መረጃ ያሳያል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የአማራ ክልል ቅርንጫፍ አሥተባባሪ ወንድምአገኝ ወዳጅ ኮሚሽኑ በክልሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ከ15 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሃድሶ ሥልጠና ማለፋቸውን ተናግረዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ በአራት ዙር ሥልጠና ወስደዋል ነው ያሉት።
የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሥራቸው መመለሳቸውን ያነሱት አሥተባባሪው በማኅበር በማደራጀት እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ወደ ግል ሥራቸው እንዲመለሱ በማድረግ የመልሶ ማቋቋም ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጎን በመኾን ሰላምን ለማጽናት እየሠሩም ነው ብለዋል።
ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ በመቀበል ችግሮችን በውይይት በመፍታት የሰላም ባለቤት መኾን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
(ፎቶ፦ ከፋይል)
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
