
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ምዕራፍ ከታቀደለት ጊዜ በፊት መሳካቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል። ለዚህም ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት፣ “በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የታቀደውን ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት ተችሏል” ብለዋል።
የ“5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች” ሐምሌ 16/2016 ዓ.ም ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ፣ በመረጃ ትንተና፣ በአንድሮይድ ሶፍትዌር ልማት እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ ትምህርቶች 5,005,146 ሠልጣኞች ተመዝግበው ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሥልጠናውን ማጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት።
ይህ ስኬት የሕዝባችንን ቁርጠኝነት እና ወሰን የሌለው አቅም ማረጋገጫ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በዲጂታሉ ዓለም በልኩ ለመዘጋጀት የጀመርነው ታሪካዊ ምዕራፍ፤ የጉዟችን ማብቂያ ሳይሆን፥ ብሔራዊ ርዕያችንን ይበልጥ የምናፋጥንበት መነሻ እንደሆነም ጠቁመዋል።
እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም ድረስ የሠልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ የተሰነቀውን ግብ ለማሳካት፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚህ ብሔራዊ ተልዕኮ አካል እንዲሆን ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ለወጣት ተማሪዎቻችን፤ መጭው የክረምት ወቅት ትልቅ ዕድላችሁ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጊዜያቸውን በዋዛ ከማሳለፍ ተቆጥበው በመመዝገብ እና በመማር ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው የዲጂታል መሪዎች እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ሥልጠናዎቹ ሙሉ በሙሉ በነጻ የሚሰጡ ሲሆን፣ የምስክር ወረቀቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ነው። “የምትገነቡት ነገ የሚጀምረው ዛሬ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቶች በቀሪ ጊዜያት በመመዝገብ ሥልጠናውን እንዲወስዱ አሳስበዋል።
#አሚኮ_ዜና #አሚኮ #ኢትዮጵያ #PMAbiyAhmed #ኢትዮኮደርስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
