
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል 539 ትምህርት ቤቶች የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ያስፈትናሉ። 99 ሺህ 897 ተማሪዎች ደግሞ ፈተናውን ይወስዳሉ።
ፈተናውን ከሚሰጡት አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች መካከል 315 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን በዲጂታል ወይም በበይነ መረብ ሥርዓት ያስፈትናሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 215 ትምህርት ቤቶች በዩኒቨርሲቲዎች የሚያስፈትኑ ሲኾን ቀሪዎቹ 100 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በራሳቸው አቅም ፈተናውን ለተማሪዎቻቸው እንደሚሰጡ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ ሀገር አቀፍ ፈተናውን በበይነ መረብ ከሚሰጡ ውስጥ ነው። ትምህርት ቤቱ በዚህ ዓመት ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን የሚወስዱ 947 ተማሪዎች አሉት። ኹሉም ተማሪዎች ፈተናቸውን በበይነ መረብ እንደሚወስዱም ከትምህርት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ከተፈታኞች መካከል ተማሪ ብርሃኑ አብነት እና ተማሪ ፀዳሉ ሞገስ ሀገር አቀፍ ፈተናውን በበይነ መረብ ለመፈተን የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲወስዱ እንደቆዩ ነግረውናል።
በትምህርት ቤቱ ኢንተርኔት እና ኮምፒዩተሮች ተሟልተውልን፥ ልምድ ያላቸው የአይሲቲ መምህራን ተመድበውልን በየቀኑ በፈረቃ ተከፋፍለን ልምምድ ስናደርግ ቆይተናል ነው ያሉት።
ከትምህርት ሚኒስቴር መለማመጃ ጥያቄዎች ያሉበት ሊንክ መላኩን ያነሱት ተፈታኝ ተማሪዎቹ ሊንኩን የመክፈት፣ የይለፍ ቃል የማስገባት እና የተቀመጡ ጥያቄዎችን በመሥራት በይነ መረቡ እየተለማመዱ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።
በፈተናው ወቅት መደናገር እንዳይፈጠርባቸው በተለይም ኮምፒውተሩን በራሳቸው ማንቀሳቀስ እንዲችሉ እና በሥነ ልቦና ዝግጁ ኾነው እንዲቀርቡ ትምህርት ቤቱ እና የአይሲቲ መምህራን አሥፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉላቸው መኾኑን አመላክተዋል።
በሀገር አቀፍ ፈተናው ጥሩ ውጤት ለማምጣት ያደረጉት ዝግጅት እንዳለ ኾኖ ፈተናውን በበይነ መረብ መውሰዳቸው አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አሳውቀዋል። ለበይነ መረብ ፈተናው በዕውቀትም፣ በሥነ ልቦናም ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ፈተናውን በበይነ መረብ መውሰዳቸው ኩረጃን በማስቀረት ተማሪዎች በተዘጋጁበት ልክ ፈተናውን እንዲሠሩ እና የደከሙበትን ውጤት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ ለአሚኮ በሰጡት መረጃ የሀገር አቀፍ ፈተናውን በበይነ መረብ ለመስጠት ክልሉ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ መቆየቱን ገልጸዋል። ፈተናውን በበይነ መረብ ለሚሰጡ ትምህርት ቤቶች ኮምፒውተሮችን፣ ላፕቶፖችን፣ ኢንተርኔት እና መሰል አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እንደሠራ መገለጹም ይታወሳል።
ቢሮው ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት በፈተና ወቅት የኢንተርኔት እና የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ እንዳይፈጠር ለማድረግ እየተሠራ መኾኑም ተገልጿል።
#አሚኮ_ዜና #ትምህርት_የፈተና_ዝግጅት
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
