በደረሰኝ አቆራረጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገው የታክስ አሥተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጅ መድረክ ተካሄደ።

8

 

አዲስ አበባ: ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዲስ እየተሻሻለ በሚገኘው የታክስ አሥተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጅ መድረክ አካሂዷል።

በአስረጅ መድረኩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ሆረታ በየጊዜው ከግብር ከፋዩ እየቀረቡ የሚገኙ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያስችል እንደኾነ ገልጸዋል።

በዚህ ረቂቅ ላይ የተሻሻሉ አዳዲስ ጉዳዮች ይገኛሉ:-

👉ነጋዴዎች በታክስ አከፋፈል እና ውሳኔ ላይ ቅሬታ ሲኖራቸው ከታክስ መስሪያቤቱ ጋር በአስማሚ ይነጋገራሉ፤ ከፍርድ ቤት በፊት ችግራቸውን የመፍታት ዕድል ያገኛሉ።

👉አንድ ደረሰኝ ያልቆረጠ ነጋዴ 100 ሺህ ብር የሚቀጣ ሲኾን በአንድ በጀት ዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ከተቀጣ በወንጀል ከ3 እስከ 5 ዓመት እስራት ይቀጣል።

👉ደረሰኝን ከዋጋው በታች የቆረጠ እና ተመሳሳይ ያልተገባ ደረሰኝ ያቀረበ ከ5 እስከ 7 ዓመት በእስራት ይቀጣል።

👉ከዚህ በፊት የነበረው አዋጅ አንድ ግብር አጭበርብሯል ተብሎ የታመነ እና ማጭበርበሩ የተረጋገጠ ግብር ከፋይ አንደገና የማጣራት ተግባር በማንኛውም ጊዜ የግብር መስሪያ ቤቶች የመመርመር ሥልጣን የነበራቸው ሲኾን አሁን በ10 ዓመት ብቻ ወደኋላ ተመልሶ የመመርመር ሥልጣን ይሰጣቸዋል።

👉አንድ ግብር ከፋይ ወደ አስማሚ እና ይግባኝ ሲሄድ 75 በመቶ የመክፈል ግዴታ የነበረበት ሲኾን አሁን የተወሰነበትን 50 በመቶ ብቻ ከፍሎ ይግባኝ ይላል።

አስማሚዎች ሕጋዊነታቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ የሚያስገድዳቸው አንቀፆች ያሉ በመኾኑ የገለልተኝነት ሁኔታ አሳሳቢ አይኾንም ተብሏል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሳለኝ ወዳጆ ይህ ረቂቅ በዋናነት የዕለት ከዕለት የግብር አሠባሠብ መሰናክሎችን እና ቅሬታዎችን ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን አብራርተዋል።

ግብር ከፋዮች በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግብር እንዲከፍሉ የመንግሥት ዓላማ በመኾኑ እና ለገለልተኝነታቸው ሲባል አስማሚዎች ከነጋዴ ተወካዮች እና ማኅበራት የሚካተቱበት ሁኔታ በአዋጁ የሚካተትበት ሁኔታ አንደሚታይ ገልጸዋል።

#አሚኮ_ዜና #አዲሱ_የግብር_አዋጅ_ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአራጣ ብድር በማኅበረሰብ እና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ ወንጀል ነው።” አቶ ብርሃኑ ጎሽም