
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ በአራጣ ብድር ወንጀል መከላከል ዙሪያ ከሚመለከታቸው አጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የአራጣ ብድር በማኅበረሰብ እና በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ ወንጀል ነው” ብለዋል።
ድርጊቱ የሰዎችን መቸገር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚደረግ የኢኮኖሚ ብዝበዛ ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት።
የአራጣ ተበዳሪዎች የሚጠየቁትን ከፍተኛ ወለድ መክፈል ሲቸገሩ ሀብት ንብረታቸውን በመሸጥ፣ ወደ መሰደድ እና መፈናቀል የሚያደርስ ማኅበራዊ ቀውስን ያስከትላል። ይህም በሰዎች ላይ የማይለቅ እዳ ጥሎ የሚያልፍ ወንጀል ነው ብለዋል።
ሕጋዊ የኾነውን የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚገታ በመኾኑም በሀገር ኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አብራርተዋል።
ወንጀሉን ለመከላከል የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ከአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጋር የምርመራ ቡድን በማደራጀት የተለያዩ ሥራዎችን ሲከናውኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።
ወንጀሉን በዘላቂነት ለመከላከል ኅብረተሰቡንም በማሳተፍ ተባባሪ እንዲኾን ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ወንጀለኞችን በሕግ ፊት በማቅረብ በአራጣ ምክንያት በማኅበረሰቡ እና በሀገር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መታደግ የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀል ምርመራ ዋና መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ዳምጤ ባዬ የአራጣ ብድር ወንጀል አሳሳቢ በመኾኑ የፖሊስ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ ቅንጅታዊ አሠራሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የምርመራ ቡድኑ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ የተሠራው ሥራ የሚበረታታ መኾኑን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የወንጀሉን አስከፊነት በተመለከተም ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሊሠራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
#አሚኮ_ዜና #የአራጣ_ብድር_ወንጀል_አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
