🕊️ የዘመናት ቁስል ፈውስ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የጋራ ዕድል !

4

 

ሀገራዊ ምክክር ሀገራትን ከከፋ የፖለቲካ ቀውስ ወደ ዘላቂ ሰላም የሚያሸጋግር ወሳኝ ድልድይ ነው። ሥር የሰደዱ እና ውስብስብ ግጭቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ሰፊ ዕድል ይሰጣል። ምክክር ጠመንጃን በውይይት፤ ጥላቻን ደግሞ በመግባባት የሚተካ የሰላም ጉዞ ነው።

ይህ ሂደት የጥቂት ልሂቃን የሥልጣን ክፍፍል ወይም ስምምነት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም መላውን ሕዝብ ያሳተፈ እና አዲስ ማኅበራዊ ውል የሚፈጠርበት ሕዝባዊ መድረክ ጭምር እንጂ።

በርካታ የዓለማችን ሀገራት ይህን ፈታኝ ግን እጅግ አስፈላጊ መንገድ በስኬት ተጉዘዋል። ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ሥርዓት ጋር በተገናኘ የገጠማትን ሀገር የመፍረስ አደጋ የቀለበሰችው በዚሁ በብሔራዊ ምክክር ነው። እ.አ.አ. በ1993 የተካሄደው ባለብዙ ፓርቲ ድርድር ለዚህ በጥሩ ማሳያነት ይጠቀሳል። ሂደቱ ያለ የውጭ አደራዳሪ ጣልቃ ገብነት በራሳቸው በደቡብ አፍሪካውያን የተመራ ሲኾን ቴክኒክ ባለሙያዎችን እና የአካባቢ ሰላም ኮሚቴዎችን በአግባቡ ተጠቅመዋል። በዚህም የሽግግር ሕገ-መንግሥት በማጽደቅ በ1994 የመጀመሪያቸውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ በቅተዋል።

በተመሳሳይ ቱኒዚያ እ.አ.አ. በ2011 ከአረብ አብዮት ማግሥት ያጋጠማትን አደገኛ መከፋፈል በብሔራዊ ምክክር አልፋዋለች። እ.አ.አ በ2013 አራት ታላላቅ የሲቪል ማኅበራትን ያቀፈው “ኳርትት” በፈጠረው የጋራ ጥምረት ችግሩን መፍታት ተችሏል። ይህም ሀገር ስትፈርስ እና ችግር ውስጥ ስትገባ ኀላፊነቱ የመንግሥት ብቻ ነው ከሚል አስተሳሰብ ወጥቶ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ያረጋገጠ ክስተት ኾኗል።

የቱኒዚያው ሂደት በጥንቃቄ የታቀደ ሳይኾን አፋጣኝ የችግር ማስታገሻ በመኾኑ የሕዝቡ ተሳትፎ ጎልቶ እንዳልታየበት መረጃዎች ያሳያሉ። ምክክሩ በዋናነት ፖለቲከኞችን እና ልሂቃንን ብቻ ያሳተፈ ቢኾንም ሀገሪቱን ግን ከከፋ ቀውስ መታደግ ችሏል።

እንደ ኮሎምቢያ፣ ኬንያ እና ጓቲማላ ያሉ ሀገራትም ከደም አፋሳሽ ግጭት የወጡት በዚሁ የውይይት ጥበብ ነው። እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የኾነ የተለየ ታሪክ ቢኖረውም የሁሉም ስኬት መነሻ ግን ቁርጠኛ የሰላም ፍላጎት ነው።

አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ የገጠማትን ውስብስብ ቀውስ ፈትታ ሀገራዊ አንድነቷን ለማጽናት ይህን ታሪካዊ እና ወሳኝ ምዕራፍ ተያይዘዋለች። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላለፉት አራት ዓመታት ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ኮሚሽኑ አሁን ላይ ስምንት ዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

የምክክር ሂደቱም ሐምሌ 8 ቀን ይጀመራል። ይህንንም ተከትሎ የሕዝብ አደራ የተቀበሉ ተመካካሪዎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየገቡ ይገኛሉ።

የብሔራዊ ምክክሮች በተካሄዱባቸው ሀገራት የተመዘገቡ ውጤቶች እና ለኢትዮጵያ የሚሰጡት ትምህርት በተመለከተ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሱራፌል ጌታሁን የተሠራው ጥናት እንደሚያሳየው ምክክሩ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ለተከማቹ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጥ ያላቸውን ጠንካራ እምነት ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከገለልተኝነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ስጋቶችን ለማስወገድ ሰፊ ጥረት አድርጓል። ከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል እስከ ልሂቃን ድረስ አጀንዳዎችን ያሰባሰበ ሲኾን፣ የተሳታፊዎችንም ልየታ በተመሳሳይ አካታች መንገድ አከናውኗል። ይህ አካታችነት የፖለቲካ ኃይሎችን፣ የታጠቁ ቡድኖችን፣ የሲቪል ማኅበራትን፣ እንዲሁም ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ሀሳባቸውን አዋጥተዋል።

በአጠቃላይ የዓለም አቀፍ ሀገራት ተሞክሮ የሚያረጋግጠው ሀገራዊ ውይይቶች በአካታችነት፣ በግልጽነት እና በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ መመራት እንዳለባቸው ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ሂደቱ በጥንቃቄ የታቀደ እና ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ሊኾን ይገባል። በመረጃ ምንጭነት የዓለም አቀፍ ምሁራን የጥናት እና ምርምር ገጽን ተጠቅመናል።

#ሀገራዊ_ምክክር #የኢትዮጵያ_ሀገራዊ_ምክክር #NationalDialogue #EthiopianNationalDialogue #የጋራ_ድልድይ
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ3_2018_ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article❌ ከአፈና እስከ ሀገር ክህደት፤ የሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን የዘወትር ባህሪ