❌ ከአፈና እስከ ሀገር ክህደት፤ የሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን የዘወትር ባህሪ

12

 

ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን በሰሜኑ የጦርነት ወቅት ያስከተለው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት በታሪክ መዝገብ ውስጥ በጥቁር ቀለም የሰፈረ አሳዛኝ ተግባር መኾኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ይህ ሕገ ወጥ ኃይል በፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሳይማር ዛሬም እናቶች የለቅሶ ካባ እንዲደርቡ፤ ሕጻናት ወላጅ አልባ እንዲኾኑ እና የበርካታ ታዳጊዎችን የነገ ተስፋ በደም አፋሳሽ ጦርነት እና በርካሽ ፖለቲካ ሕይወት መቅጠፉን ቀጥሎበት ይገኛል።

​ሕገወጡ ቡድን በሰሜኑ ጦርነት የፈጸመው ድርጊት ዘመን የማይሽረው እና ታሪክ ይቅር የማይለው ታላቅ ቁስል ቢኾንም የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና የዜጎች ሕይወት መጥፋትን ለማስቀረት ሲል የሰላም አማራጮችን እና ድርድሮችን በመጠቀም የሰላም በር ከፍቶ የፕሪቶሪያ ስምምነት መደረጉም ይታወሳል።

ነገር ግን ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ይህን ስምምነት አፍርሶ ከውጭ እና ከውስጥ ኃይሎች ጋር ጥምረት ፈጥሮ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ መኾኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አበራ ታደሰ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በማስቆም ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የስምምነቱ አለመተግበር እና ዳግም የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙ እጅግ አሳሳቢ ነው ብለዋል። በተለይም በትግራይ ክልል ወጣቶች እየታፈሱ ወደ ትጥቅ እንዲገቡ መደረጉ የክልሉን ሰላም ወደ ቀድሞው የግጭት አዙሪት የሚመልስ አደገኛ ምልክት እንደኾነ ነው የገለጹት።

ይህ ዳግም ለግጭት የመነሳሳት ሂደት ለክልሉ ብቻ ሳይኾን በጥቅል ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው ብለዋል። ቡድኑ ያለው የፖለቲካ ባሕል በንግግር ላይ የተመሠረተ አለመኾኑ የተጀመረውን የሰላም ጉዞ ወደ ኋላ የሚጎትት እንደኾነም ገልጸዋል።

ከዚህም በላይ ሕገ ወጡ ቡድን ከውጭ ኃይሎች ጋር የሚያደርገው ያልተገባ ትስስር ሀገርን ለአደጋ የሚያጋልጥ፣ በሉዓላዊነት የተቃጣ እኩይ ድርጊት መኾኑን ነው ያነሱት። ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር ወደ ኋላ የሚጎትት ነው ብለዋል።

በዚህም መንግሥት የሀገርን ሰላም እና ደኅንነት የመጠበቅ ኀላፊነት አለበት ያሉት መምህሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በጠረንጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

​የሀገርን ሕልውና ማስጠበቅ የመንግሥት ብቻ ሳይኾን የእያንዳንዱ ዜጋ የጋራ አሻራ የሚያርፍበት ጉዳይ እንደኾነም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገር ላይ የተነሳውን አኩይ ድርጊት ለመመከት በአንድነት ከመንግሥት ጎን በመቆም፣ የሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ማውገዝ ይኖርበታል ብለዋል።
ሕገ ወጥ ቡድኑ የፕሪቶሪያ ስምምነትም በማፍረሱ የአፍሪካ ኅብረት፤ የአውሮፓ ኅብረት እና አጠቃላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአንድ ድምፅ ማውገዝ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የትግራይ ሕዝብ ሰላም ፈላጊ ነው፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ እናቶች እና ሴቶች የሚያሳዩት ተቃውሞ የሰላም ጥማቸውን የሚያሳይ በመኾኑ ይህንን አቋም መደገፍ እና ለአፈና የተጋለጠውን ሕዝብ በባለቤትነት መታደግ እንደሚገባም አንስተዋል።

​ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በሰላም የምትፈታበት የፖለቲካ ባሕል እንዲዳብር እና የተጀመረው የሰላም ሂደት ሳይደናቀፍ ሀገርን የሚያፈርስ አፋኝ አካሄድ እንዲቆም በጋራ መነሳት ግድ ይላል ብለዋል።

#የፕሪቶሪያ_ስምምነት #ሰላም_ለኢትዮጵያ #የሰላም_ሂደት #PretoriaPeaceAgreement #PeaceForEthiopia
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ3_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበምሥራቅ እዝ አንድ ኮር የሠራዊቱ መሪዎች ከእስቴ ወረዳ ማኅበረሰብ ጋር ችግኝ ተክለዋል።
Next article🕊️ የዘመናት ቁስል ፈውስ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የጋራ ዕድል !