
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበራዊ ሚዲያ ትንኮሳ በእንግሊዝኛ Cyberbullying ማለት ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚፈጸም የማዋከብ ድርጊት ነው። በአብዛኛው ታዳጊዎችን ዒላማ ያደረገ የሳይበር ጥቃትም ነው።
ይህ ዓይነቱ ጥቃት በማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ በመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች፣ በበቪዲዮ መጫዎቻ የኢንተርኔት መድረኮች እና በሞባይል ስልኮች ላይ ሊከሰት ይችላል።
ድርጊቱ ኾን ተብሎ ስም ለማጥፋት፣ ለማስፈራራት፣ ለማስቆጣት ወይም ለማዋረድ ታስቦ በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም ከዩኒሴፍ ድረ ገጽ ላይ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
✍️ዋና ዋና ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው?
#በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለ አንድ ሰው የሐሰት ወሬዎችን መዝራት ወይም ሰዎችን ሊያሳፍሩ ወይንም ሊያሸማቅቁ የሚችሉ ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን መለጠፍ።
#በመልእክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች አማካኝነት ጎጅ፣ ተሳዳቢ ወይም አስፈሪ የኾኑ ጽሑፎችን፣ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን መላክ።
#የሌላ ሰውን ማንነት በመጠቀም ወይም በሐሰተኛ አካውንት (Fake Account) አማካኝነት ሌሎችን የሚያስቀይሙ መልእክቶችን መላክ።
#በየጊዜው የሚዘምኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን (Generative AI) በመጠቀም ጾታዊ ትንኮሳዎችን ወይም የሳይበር ማዋከብ ድርጊቶችን መፈጸም።
👉የጥቃቱ ሰለባ ልጆች የስሜት መረበሽ (ለዲፕሬሽን) እና ለተለያዩ የጭንቀት እክሎች ሊጋለጡ ይችላሉ።
በተጨማሪም የጓደኝነት ግንኙነታቸው መቀነስ፣ ከትምህርት ቤት ሕይወት ጋር መላመድ ሊከብዳቸው ይችላል፤ በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ላይ ያላቸው እምነትም ሊጠፋ ይችላል።
✍️እንዴት መከላከል እና ማስቆም ይቻላል?
#ልጆች ወይም ታዳጊዎች የኢንተርኔት ጥቃት ሲደርስባቸው ለወላጆቻቸው፣ ለአስተማሪዎቻቸው ወይም ለሚያምኑት ሰው በአስቸኳይ መናገር አለባቸው። ወላጆችም የልጆቻቸውን ባሕርይ በመከታተል ቀድመው ሊደርሱላቸው ይገባል።
#የሚላኩ የጽሑፍ መልዕክቶችን፣ የተለቀቁ ምስሎችን እና ጥቃቶችን በፎቶ ወይም በስክሪንሻት (Screen shot) በመመዝገብ ለሕግ አካል ማቅረብ ይገባል።
#ለአጥቂው ምላሽ አለመስጠት እና ችላ ማለት ኃይል ያሳጣዋል። ከሁሉ የተሻለው አማራጭ ጥቃት አድራሹን ከማኅበራዊ ሚዲያ እና ከኢሜይል አካውንት ላይ ሙሉ በሙሉ ማገድ ይገባል።
#ወላጆች ልጆቻቸው በኢንተርኔት እና በስልኮቻቸው ላይ ምን እያደረጉ እንዳሉ ሊከታተሉ ይገባል።
👉.የማኅበራዊ ሚዲያ ትንኮሳ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ብቻ ሳይኾን በኢሜይል፣ በስልክ መልዕክት እና በቪዲዮ ጌም መተግበሪያዎች ጭምር ሊከሰት እንደሚችል ማወቅ እና መጠንቀቅ ተገቢ ነው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
