በአማራ ክልል የጎርፍ አደጋን ለመከላከል 157 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል።

6
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በየዓመቱ የክረምት ወቅትን ተከትሎ ቀላል የማይባሉ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በጎርፍ የመጠቃት ችግር ሲገጥማቸው ይስተዋላል።
በየዓመቱ የችግሩ ሰለባ ከኾኑ የክልሉ አካባቢዎች መካከል ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን ሥር የሚገኙት ሊቦከምከም እና ፎገራ ወረዳዎች ይጠቀሳሉ።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሊቦ ከምከም እና የፎገራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደሮች ቀደም ሲል በክረምት ወቅት አካባቢያቸው በድንገተኛ ጎርፍ ይጠቃ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህም ለሰው ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት ውድመት ይዳርግ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ በተለይም ሕጻናት እና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የጉዳቱ ሰላባ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
በዚህ ዓመት ግን ከበፊቱ የተሻለ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት የሚያደርጉ ሥራዎች እንደተሠሩላቸው ገልጸዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኑነት ባለሙያው አበባው አየነው የክልሉ መንግሥት በፎገራ እና በሊቦ ከምከም ወረዳዎች 14 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ የጎርፍ አደጋ የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህም ኾኖ ችግር ቢከሰት እንኳን ማኅበረሰቡ እንዴት መከላከል እንዳለበት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እና ተያያዥ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖር ለማድረግ እና ማኅበረሰቡ በየጊዜው የጎርፍ አደጋ ጉዳት ሰለባ እንዳይኾን ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ለመሥራት የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሰርክአዲስ አታሌ በአማራ ክልል በመጭው የክረምት ወቅት በጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል 157 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ባለፈው የ2017/2018 በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመቀናጆ በጀት 157 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ የጎርፍ አደጋ ስጋቱን ለመከላከል ሥራ መከናወኑንም አስታውሰዋል፡፡
በአብነትም ቁጥራቸው ከ200 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከጎርፍ አደጋ ለመጠበቅ መሠራቱን ገልጸዋል።
በተያዘው ዓመት ደግሞ በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች እና 16 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ መከላከል ሥራዎች እንደሚሠራ ነው ያመላከቱት።
በሚሠሩ የጎርፍ አደጋ የመከላከል ሥራዎች ላይ አጋር አካላት እና የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ፎቶ፦ ከአማራ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከደብረ ታቦር እስከ ሩሲያ የዘለቀው የህልመኞቹ ተመራማሪ ታዳጊዎች የስኬት ዕውቅና !
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላለፉ።