
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለጋራ ዓላማ የሚተጉ፤ ካጋጠሟቸው መሰናክሎች ይልቅ ትልቁን ራዕይ የሚያዩ እና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ኾነው እርስ በርስ የሚደጋገፉ ታዳጊዎች ሁልጊዜም ለሀገር ትልቅ ተስፋዎች ናቸው።
የዛሬ ባለታሪኮቻችን ከተለያዩ ማሕጸኖች የተገኙ ነገር ግን በአንድ የፈጠራ መንፈስ የተሳሰሩ ድንቅ ሁለት ታዳጊዎች ናቸው። ታዳጊዎቹ በደብረ ታቦር ከተማ ይገኛሉ።
ዮሐንስ መልካሙ ከዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ብሩክ አበባው ከዳንሻ ቤዛዊት ዓለም አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ታዳጊዎች ናቸው።
ግንኙነታቸው ከአንደኛ ክፍል የጀመረው ይህ ጥምረት በትምህርት ቤት ውስጥ አንዱ አንደኛ ሌላኛው ሁለተኛ እየተባባሉ በመፈራረቅ የዘለቀ የውድድር እና የመደጋገፍ ጉዞ አላቸው። ዛሬ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ቢማሩም የፈጠራ ህልማቸው ግን በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል ውስጥ አገናኝቷቸዋል።
እነዚህ ታዳጊዎች የሀገራቸው እና የአህጉራቸው ስጋት የኾነው “የማዳበሪያ እጥረት” አሳስቧቸዋል። ለፈጠራ መነሻ የኾናቸውም ይሄው ጉዳይ ነው። ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በአፈር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በማለም በፀሐይ ኃይል (ሶላር) የሚሠራ ዘመናዊ የማዳበሪያ ማምረቻ ማሽን ፕሮቶታይፕ ሠርተው በተግባር አሳይተዋል።
ይህ ማሽን በአካባቢ የሚገኙ የምግብ ትርፍራፊዎችን፤ ቅጠላቅጠሎችን እና ሌሎች ደረቅ ቆሻሻዎችን በመጠቀም ከሰው ንክኪ ነጻ የኾነ ኦርጋኒክ ማዳበሪያ እንዲመረት የሚያደርግ ነው።
የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የሚሠሩት ይህ ጥበብ የታከለበት የፈጠራ ሥራ ለችግር መፍትሔ ፍለጋ የተደረገ ድንቅ ጥረት ነው ማለት ይቻላል።
ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የፈጠራ ሥራዎች የልጅነት ህልማቸው እንደነበር የገለጹት ታዳጊዎቹ ገና በልጅነታቸው በትምህርት ቤት የተለያዩ ፈጠራዎችን ይሠሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
በትምህርት ቤት፤ በወረዳ እና በዞን ደረጃ ተሳትፈው ያካበቱት ልምድ የፈጠራ ጉዟቸውን አጠናክሮታል።
የታዳጊዎቹ የፈጠራ ጉዞ ድንበር አልገታውም።
በ2017 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴር ሀገር አቀፍ የውድድር መድረክ ላይ አንደኛ በመውጣት ኢትዮጵያን ወክለው በሩሲያ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የፈጠራ ኦሎምፒያድ (Environmental Protection) ዘርፍ ተሳትፈዋል።
በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ በግል ደረጃ ብሩክ ሁለተኛ በመኾን የብር፣ ዮሐንስ ደግሞ ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በቡድን ደረጃም የዲፕሎማ (የክብር ማዕረግ) ተሸላሚ ኾነዋል።
በተወዳደሩበት ዘርፍ የመጀመሪያ እንደኾኑ የገለጹት ታዳጊዎቹ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ሀገር አኩርተው ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋል፤ አስጠርተዋልም።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ወጪያቸውን በመሸፈን ለዚህ ስኬት እንዲበቁ እንዳገዛቸውም ታዳጊዎቹ ተናግረዋል። ህልማችን አላበቃም ጉዟችን ይቀጥላል ሲሉም ገልጸውልናል።
አሁንም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን እየሠሩ ነው። ለወደፊቱም እነዚህን የፈጠራ ሥራዎች ወደ ማኅበረሰቡ ለማውረድ እና ወደ ገንዘብ ለመቀየር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተውልናል። በስፔስ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የመሠማራት ህልም እንዳላቸውም ነግረውናል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተሩ ታደሰ ዋለልኝ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ለኅብረተሰቡ ችግር ፈቺ የኾኑ ቴክኖሎጂዎችን የግብርና ምርታማነት ማሳደጊያ፤ የኑሮ ማሻሻያ እና አካባቢ ጥበቃ ሥራን ወደ ተግባር በማስገባት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎቹ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የፈጠራ አቅማቸውን እያሳደገ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የምርምር ውጤቶች በወረቀት ላይ ብቻ እንዳይቀሩ ከመነሻቸው የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት መሠረት በማድረግ እና የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘቡ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
ይህ የሁለቱ ታዳጊዎች ስኬት ለሌሎች ታዳጊዎችም አርዓያ የሚኾን ድንቅ ምሳሌ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
