ወልድያ አሁን በለውጥ ላይ መኾኖን ነዋሪዎቿ ተናገሩ።

19
ወልድያ: ሰኔ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወልድያ አቧራዋን አራግፋለች፤ ወልድያ ያረጀ ገጽታዋን ቀይራለች፤ ወልድያ ያልተመቹ ጎዳናዎቿን አስተካክላለች። ለዘመናዊ ከተማ የማይመጥኑ የነበሩትን ቀይራ ተውባለች።
አሁን የወልድያ ከተማ ጎዳናዎች አምረዋል። ሳቢ እና ማራኪ ኾነዋል። ለነዋሪዎቿ የማይመቹት መንገዶች ተስተካክለዋል።
የወልድያ ከተማ ነዋሪዎችም በከተማዋ መለወጥ መደሰታቸውን ገልጸዋል። አቧራ ይበዛባት፤ ተሽከርካሪ እና እግረኛ በአንድ ጎዳና ይሄዱባት የነበረችው ወልድያ ተለውጣለች ነው ያሉት። ወልድያ አሁን ላይ በለውጥ ላይ ናት፤ አምራለች፤ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች ተሠርተውላታል ብለዋል።
አሁን ላይ ተሽከርካሪ እና እገረኛ በአንድ ጎዳና መንቀሳቀስ ቀርቷል፤ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች በአግባቡ ተሠርተዋል ነው ያሉት። አረንዴ ሥፍራዎችም ለከተማዋ ውበትን ያላበሱ እና ለነዋሪዎችም መዝናኛ የኾኑ ናቸው ብለዋል። የተሠራውን ልማት መጠበቅ እንደሚገባም አንስተዋል።
የወልድያ ለውጥ ፈጣን እና የሚገርም ነው ብለዋል። ይሄን ለውጥ በማየታችን ደስተኞች ነን፤ ወልድያ የተለየች ከተማ ኾናለች፤ ማታ ማታ ትናፍቀናለች ነው ያሉት።
ወልድያ ማራኪ በኾነ መንገድ ተገንብታለች ብለዋል። ወልድያን በትብብር ከዚህ የበለጠ ማልማት ከእኛ ይጠበቃል፤ ወልድያን አስውበን ለትውልድ ማሸጋገር አለብን ነው ያሉት። ወልድያ ላይ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እና የከተማዋን ኢኮኖሚ የሚያነቃቁ ዘመናዊ ሼዶችም መገንባታቸውን ገልጸዋል።
ወልድያ እውነትም መለወጧን የሚረዳው የድሮ ገጽታዋን ያየ ነው ብለዋል። በወልድያ መለወጥ ደስተኞች ነን፤ የወልድያን ውበት እና ለውጥ አለማድነቅ አይቻልም ነው ያሉት። ልማቱ የጋራችን ነው፤ የጋራ ልማታችንን ጠብቆ ማቆየት እና የበለጠ ማልማትም ይጠበቅብናል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የልማት ሥራዎችን ለመመልከት በወልድያ ከተማ ተገኝተዋል።
Next articleከደብረ ታቦር እስከ ሩሲያ የዘለቀው የህልመኞቹ ተመራማሪ ታዳጊዎች የስኬት ዕውቅና !