የማዕድን ሀብትን በሳይንሳዊ ዕውቀት እና በዘላቂነት ለመጠቀም ጥናትን እንደ ድልድይ መጠቀም ይገባል።

13

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ በክልሉ ከሚገኙ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሥነ-ምድር ጥናት፣ ካርታ ሥራ እና የማዕድን ፍለጋ ጥናት ለማካሄድ የሚያስችል ይፋዊ የውል ስምምነት አከናውኗል።

ስምምነቱ የተካሄደው ከባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ወልዲያ፣ ወሎ፣ ደብረ ብርሃን እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው።

የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ኃይሌ አበበ ስምምነቱ ተራ የሰነድ ልውውጥ ሳይኾን የክልሉን እና የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በሳይንሳዊ ዕውቀት እና በዘላቂነት ለመጠቀም የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን ድልድይ ነው ብለዋል።

አቶ ኃይሌ ቢሮው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የወሰነባቸውን በርካታ ምክንያቶች ሲያብራሩ እንዳሉት፦

👉 በክልሉ በተደረገው መለስተኛ ጥናት ከፍተኛ የማዕድን ሀብት መኖሩ በመረጋገጡ የማዕድን ባለሀብትነትን በጋራ ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረገ ነው።

👉 ከግብርና በመቀጠል ማዕድንን የክልሉ ሁለተኛው የሀብት ምንጭ ለማድረግ መንግሥት በወሰደው አቋም መሠረት ሀገር በቀል ኢኮኖሚን ለመገንባት ያስችላል።

👉 በንድፈ-ሐሳብና በተግባር መካከል ያለውን ክፍተት ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ እና በዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሩ የምርምር ውጤቶች በተግባር ወርደው የሕዝብን ሕይወት እንዲቀይሩ ብሎም ባለሀብቶች በጥናቶቹ ተማምነው በልበ ሙሉነት በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ ታሳቢም ያደረገ ነው።

👉 የማዕድኑን ዘርፍ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በጥናት ላይ በተመሠረተ መረጃ ለመምራት እና የመረጃ አሥተዳደርን ለማዘመን ዋና ዋና አነሳሽ ምክንያቶች ናቸው።

አሁን ያለው የዓለም ሁኔታ የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂ እና የማዕድን ፉክክር የበላይነት የያዘበት በመኾኑ ይህ በወረቀት ላይ የሰፈረው ስምምነት በተግባር ተተርጉሞ ፍሬ እንዲያፈራ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ዋና ጸሐፊ ጀጃው ደማሙ (ዶ.ር) እንደገለጹት የማዕድን ቢሮ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በጀመረው የተቀናጀ አሠራር የክልሉን የተፈጥሮ ሀብቶች በጥናት በማረጋገጥ አዲስ ተስፋ መፍጠር ነው ብለዋል። ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ትልቅ አቅም መኾኑንም ጠቁመዋል።

የዘርፉን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ተሳትፎውን በባለሙያዎች ብቻ ሳይገድቡ ሰፊ የሀብት አቅም ያላቸውን አካላት እና ሌሎች አጋር ድርጅቶችን ማካተት ያስፈልጋል ብለዋል። ፎረሙም የተጀመሩትን የምርምር እና ልማት ሥራዎችን ለማሳካት ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል።

#አሚኮ_ዜና #የማዕድን_ልማት_ጥናት_አማራ_ክልል _ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ።
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የልማት ሥራዎችን ለመመልከት በወልድያ ከተማ ተገኝተዋል።