የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኀይል መቆራረጥን ለማስቀረት እየሠራ ነው።

12

 

አዲስ አበባ: ሰኔ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥን ለመቀነስ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።

አገልግሎቱ የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ እና የክረምት ዝግጅትን በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኀን መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም እየተስተዋለ ያለውን የኀይል መቆራረጥ በዘላቂነት ለመቀነስ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ እና ያረጁ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን በመለየት በከፍተኛ ወጭ የመልሶ ግንባታ እና ማሻሻያ ሥራዎች እያከናወነ መኾኑን ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያብራራው።

የአገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት አሥተዳደር መሪ ሥራ አሥፈፃሚ ገበየው ሌካሳ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን የኀይል መቆራረጥ ለመቀነስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ እየሠራ መኾኑን አመላክተዋል። የኀይል መቆራረጥ መንስኤዎችን በመለየትም ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

በተደረጉ ጥናቶች መሠረት 92 በመቶ የማሰራጫ ኔትወርክ፣ 86 በመቶ ደግሞ ማሰራጫ ትራንስፈርመሮች የሚኾኑት ተለይተው የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ከኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ጋር ንክኪ የነበራቸውን ዛፎች ቆረጣ ማካሄዳቸውን የገለጹት መሪ ሥራ አሥፈፃሚው ዛፎች በመቆረጣቸው በየዓመቱ ሊከሰት የሚችለውን የኀይል መቆራረጥ ድግግሞሽን በአዲስ አበባ ከተማ 23 ነጥብ 8 በመቶ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የኀይል መቆራረጥን ለማስቀረት በተለይም በዝናብ ምክንያት የሚመጡ አደጋዎችን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር የ100 ቀናት ዕቅድ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

መሪ ሥራ አሥፈፃሚው አገልግሎቱ በመጭው የክረምት ጊዜ የመብራት መቆራረጥን ለመቀነስ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን ማጠናከር፣ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን ማቀላጠፍ እና ኔትወርክን የማዘመን ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠሩም አመላክተዋል።

#አሚኮ_ዜና #የኤሌክትሪክ_መቆራረጥን_ማስቀረት_ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትግበራ እውቅና የሚሰጠው ነው” የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም
Next articleቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ።