
ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አንቺ የተራራ ሥር ጌጥ፤ የኮረብታ ግርጌ ፈርጥ ነሽ፤ ስምሽ ከተራራዎች ገዝፎ ይነሳል፤ ታሪክሽ ከተራራዎች ልቆ ይወሳል።
ተራራዎችሽ መጻፍ ቢችሉ ኖሮ ጥቁር ውኃ ቀለምን፤ መቻሬ ሜዳን ብራና አድርገው ይጽፉልሽ፤ ታሪክሽንም ለመጣ ለሄደው ያሳዩልሽ ነበር። ነገር ግን ይሄን አልታደሉም፤ ዝም ብለው ይጠብቁሻል እንጂ።
በእርግጥ ዛሬም ለዘመናት አብረውሽ ቆመው ታሪክሽን በዝምታ ውስጥ ይናገራሉ፤ ጥንታዊነትሽን ይመሰክራሉ፤ ያሳለፍሻቸውን የመከራ እና የደስታ ጊዜያት ይገልጣሉ።
አንቺ ፍቅር የሚሸመትብሽ፤ አብሮነት የሚሸመንብሽ፤ ታሪክ የሚነገርብሽ፤ አንድነት የደረጀብሽ፤ ተራራዎች እንደ ታማኝ አገልጋይ በእርጋታ ቆመው ለዘመናት የሚጠብቁሽ፣ በቃል ኪዳን ጸንተው ለዘመናት ጋሻ ኾነው የቆሙልሽ፤ ጥላ ኾነው የጋረዱሽ፣ ሩህሩህ እና ደግ የሚበቅልብሽ፤ ጀግና እና ኩሩ የሚወለድብሽ የቆንጆዎቹ ከተማ እንደምን ባጅተሻል ?
አንቺ ተራራዎች ያማረውን ካባ የደረቡብሽ፤ በተራራዎች ሥር ያጌጥሽ፤ የዘመናት ታሪክ የከተመብሽ፤ የኢትዮጵያዊነት መልክ የሚገለጥብሽ፤ ኢትዮጵያውያን በእቅፍሽ ውስጥ የሚኖሩብሽ፤ የደግነት ለዛ የሚታይብሽ፤ የፍቅር አዳራሽ የተገነባብሽ የደጋጎቹ ከተማ እንኳን ደስ ያለሽ።
የቀይ ባሕር ነጋዴዎች ግመሎቻቸውን እየሳቡ መጥተው የሚያርፉብሽ፤ በአዳራሽሽ የሚሰነብቱብሽ፤ ከደንከል በረሃ እስከ መረብ ምላሽ ያሉ ኢትዮጵያውያን በፍቅር የሚገናኙብሽ፤ የእውነት የሚተሳሰቡብሽ፤ የእውነት የሚደሰቱብሽ፤ በደስታሽ የሚደሰቱብሽ፤ በሀዘንሽም የሚያዝኑልሽ፤ በችግር ጊዜ የማይክዱሽ የመተማመን ከተማ እንደምን ከርመሻል?
የስሜን መገናኛ የተባልሽ፤ አበው ከተመረጠው እና ከተመቸው ሥፍራ የከተሙሽ፤ በአራቱም ንፍቅ ለንግድ የተመቸሽ፤ ተፈጥሮ እና ታሪክ ተባብረው ያከበሩሽ፤ ስምሽን ከፍ ከፍ ያደረጉልሽ ወልድያ ኾይ ስትናፈቂ ከርመሻልና እንደምን ከረምሽ ?
ወይዛዝርቱ ሽንጣቸውን አሳምረው፤ በባሕል ቀሚስ ተውበው፣ በሚያረግደው ወገባቸው ላይ መቀነታቸውን ሸብ አድርገው፤ ጎበዛዝቱ ጎፈሬያቸውን ከምክመው በጎዳናዎችሽ የሚመላለሱብሽ፤ ባሕል፣ ታሪክ እና ሃይማኖት ተባብረው የሚኖሩብሽ፤ የታሪክ እና የአብሮነት ከተማዋ እንደምን አለሽ ?
አንቺ እብሪተኞች በጦርነት ያደቀቁሽ፤ ሃብትሽን የዘረፉብሽ፤ ልጆችሽን ያሰቃዩብሽ፤ በታሪክሽ ልክ ያላደግሽ፣ ለዓመታት ተረስተሽ የኖርሽ፤ በተራራዎችሽ ተጠልለሽ ደጉን ጊዜ የጠበቅሽ የመታገስ ከተማ እንኳን ደስ ያለሽ።
አሁን ጎዳናዎችሽ ተውበዋል፤ ጌጦችሽ አብርተዋል፤ ቆሽሸው የኖሩት ጸድተዋል፤ የተዳፈኑት ተገልጠዋል፤ ከውበት ላይ ውበት፣ ከግርማ ላይ ግርማን ደርበሻል፤ ከአረጀ እና ከአፈጀ የከተማ አሠራር ጋር ተለያይተሻል፤ አሁን ዘመኑን መስለሻል፤ ዘመኑንም ዋጅተሻል።
አሁን እንዳትነሳ አድርገን ጣልናት ያሉሽን ጥለሻቸው ተነስተሻል፤ ለክብርሽ የማይመጥነውን፤ ለታሪክሽ የማይኾነውን አራግፈሻል። አሁን ካባውን ደርበሻል፤ ዘውዱንም ደፍተሻል።
የጀግኖቹን መዳረሻ፤ የልዑላኑን መናገሻ ወልድያን የኮሪደር ልማት ገልጧታል። ታሪኳን በሚመጥን መልኩ አስጊጧታል። አሁን ወልድያ በአዲስ መልክ እና ገጽታ ተገልጣለች። በእርግጥ በወልድያ ኮሪደር ብቻ አይደለም የተሠራው ከተማውን የሚያስውቧት፤ እድገቷን የሚያፋጥኑላት ሌሎች የልማት ሥራዎችም ተሠርተዋል እንጂ።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ከተማዋ ከብስቁልና ወጥታ ወደ ልማት መጥታለች ይላሉ። ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ ኮሪደር የሠራችው ወልድያ ከተማ ውበቷን በተገቢው መንገድ ገልጣለች።
የኮሪደር ልማቱ ብዙ ጸጋዎችን በውስጡ የያዘ የሚያስደንቅ ሥራ ነው። የኮሪደር ልማቱ የሚቀጥለውን ዘመን ያሰበ፤ በተገቢው መንገድ ታቅዶበት የተገነባ፤ ዛሬ እና ነገን የሚያስተሳስር ነው ይላሉ።
ዛሬ ወልድያ ለነዋሪዎቿ ምቹ ኾናለች፤ ሕጻናት እንደ አሻቸው የሚጫወቱባት፤ አረጋውያን ጉልበታቸውን አሳርፈው ሃሴት የሚያደርጉባት፣ ትዝታቸውን ከዛሬያቸው ጋር እያጋመዱ የሚጨዋወቱባት ኾናለች ይሏታል።
የወልድያ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ ብቻ አይደለም የቀየሩት፤ የከተሜነት እሳቤ ተቀይሯል፤ የሥራ ባሕል እና መንፈስ ዳብሯል።
የወልድያን ልማት የሠራነው ዝም ብለን አይደለም፤ በአንድ እጃችን ሰላምን እያስከበርን ነው ይላሉ። የወልድያን ልማት የጸጥታ ችግር አያስቆመውም፤ ልማቱ ወልድያን ከብልጽግና ጉዞ ማስቀረት እንደማይቻል የተረጋገጠበት የመሪዎች አና የሕዝቡ ቅንጅት የታየበት ነው ብለዋል።
የሰሜኑ ጦርነት ወልድያን ጎድቷታል፤ ነገር ግን ከልማት አላስቀራትም፤ በእልህ እና በቁጭት ተነስተን እንድንሠራት አድርጎናል፤ የጦርነት አስከፊነት የሰላምን ዋጋ ለመረዳት አስችሏል፤ ወጣቶች ግጭትን ጠልተዋል፤ ለሰላምም ቆመዋል ይላሉ።
የወልድያ ሕዝብ የሚፈልገው ጠንካራ መሪ ነው፤ ጥሩ አድርገው ከመሩት በቁጭት ይከተላል፤ ጦርነትን ሳንፈራ፣ እየተጋፈጥን ልማታችንን ሠርተናል ነው የሚሉት። የሰሜኑ ጦርነት ጎድቶናል ነገር ግን አላሸፈንም ይላሉ።
አሁን ወልድያ ቁጭት የገነባት፤ መገፋት የበለጠ በእልህ ያስነሳት ውብ ከተማ ኾናለች። ሂዱ የተራራውን ሥር ጌጥ ተመልከቷት፤ የኮረብታዋን ግርጌ ፈርጥ አስተውሏት፤ በእቅፏ ሰንብቱባት፤ ፍቅርን እያስተማረች፤ አብሮነትን እያለበሰች በማይሰስት እጇ ታስተናግዳችኋለች፤ ፍቅርን እና አብሮነትን ታሳያችኋለች።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
