
ጎንደር: ሰኔ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ40 ሄክታር መሬት 25 ሚሊዮን የፍራፍሬ እና የቡና ችግኝ ለመትከል መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው በጎንደር ቀጣና ያለውን የፍራፍሬ ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ በጎንደር ከተማ ለባለድርሻ አካላት ሥልጠና ሰጥቷል።
ሥልጠናውን የወሰዱት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን፣ የሰሜን ጎንደር ዞን እና የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞኖች ግብርና መምሪያ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ናቸው።
የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ከአካባቢው ፍጆታ ባለፈ እስከ ክልል ከተማ እንደሚልኩ የነገሩን የላይ አርማጭሆ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ ደጀን ቦጋለ በቀጣይ ወራት በሦሥት የችግኝ ጣቢያዎች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
የሙዝ እና የፓፓያ ምርት በስፋት ለማልማት እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ያነሱት ደግሞ በምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አሰፉ ይመር ናቸው።
በመገባደድ ላይ ባለው በጀት ዓመት ከ2 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኝ ለመትከል የዝግጅት ሥራ ተጠናቅቋል ያሉት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሴ ማለደ ከ100 ሄክታር መሬት በላይ የአቮካዶ ችግኝ ለማልማት መታቀዱንም ጠቁመዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበራ አደባ አርሶአደሮች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን በመረዳት አትክልት እና ፍራፍሬን በስፋት እያለሙ ነው ብለዋል።
እንደ ክልል በ40 ሄክታር መሬት 25 ሚሊዮን የፍራፍሬ እና የቡና ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መድረጉን የነገሩን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በሁሉም ቦታዎች የፍራፍሬ ምርት እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የፍራፍሬ ምርት ትኩረት የሚፈልግ በመኾኑ ሁሉም ኀላፊነት ወስዶ ሊሠራ እንደሚገባ ምክትል ቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል። በችግኝ ጣቢያዎች የሚፈሉ ፍራፍሬዎች በክላስተር እንዲለሙ ማድረግ ይጠበቃልም ነው ያሉት ።
ዘጋቢ፦ ማኅደር አድማሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
