
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለዓመታት መከላከል ላይ ትኩረት አድርጋ ሥትሠራ ቆይታለች። የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በመከላከል እና በመቆጣጠር ስኬታማ ተግባራትን አከናውናለች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሽታን መከላከል ብቻ ሳይኾን አክሞ የማዳን አቅሟም ከፍ ብሏል።
ለአብነት በዓለም አቀፍ ዘንድ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የኮሮና ወረርሽኝን በመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንዳያደርስ አድርጋለች።
በቅርቡ የተከሰተውን የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝን በፍጥነት በመቆጣጠር እና በማከም ያስመዘገበችው ስኬት በዓለማቀፍ ደረጃ ምሥጋና እንዲቸራት አድርጓል። ይህም ኢትዮጵያ የማከም አቅሟን እንዳሳደገች እንደ ማሳያ ይጠቀሳል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከጀርመን ኤምባሲ ከሮበርት ኮች ኢንስቲትዩት እና ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር የአደጋ ጊዜ የሕክምና ቡድኖች ተነሳሽነት እና አጋርነት በተመለከተ ውይይት ባደረጉበት ወቅት የጀርመን አምባሳደር ብርጊት ኦሪ ኢትዮጵያ የተጠናከረ የአደጋ ጊዜ ምላሽ አቅም በመገንባቷ የማርበርግ ቫይረስን ጨምሮ የቅርብ ጊዜ ወረርሽኞችን ውጤታማ በኾነ መንገድ መከላከል መቻሏ የሚያስደንቅ መኾኑን ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በሽታን ቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት አድርጋ ሥትሠራ መቆየቷን ገልጸዋል።
በጤናውን ዘርፍ የፖሊሲ ሪፎርም ለውጥ በማድረግ መከላከል እና ማከም ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች መኾኑንም ተናግረዋል።
የጤና መሠረተ ልማቶችን በማስፋት፣ የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ፣ የመድኃኒት አቅርቦትን ቀልጣፋ በማድረግ፣ ዘመኑን የዋጀ የሕክምና ቁሳቁስ በማሟላት እና የተለያዩ አዋጆችን በማጽደቅ የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት መሠራቱን ገልጸዋል።
ተደራሽነት፣ አገልግሎት፣ ጥራት እና ፍትሐዊነት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ለሀገር ብሎም ለአህጉር አቅርቦት የሚያገለግል መድኃኒትን በሀገር ውስጥ ለማምረት መሠራቱንም ገልጸዋል።
በጄኔቫ በተካሄደው 79ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ኢትዮጵያ የእናቶችና ሕጻናት ሞትን በመቀነስ ረገድ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።
በቀጣይም የጤና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ለመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ጠንካራ የጤና ሥርዓት እንዲፈጠር በትጋት እንደሚሠራም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ሥብሠባ ላይ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ማምረት አቅም ከነበረበት 4 በመቶ ወደ 45 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ተደርጎ መሠራቱን ተናግረዋል። በ2018 በጀት ዓመት ለአጠቃላይ መድኃኒት ግዥ 70 ቢሊዮን ብር እና ለሕክምና መሣሪያዎች ግዥ ደግሞ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ተናግረዋል።
በቀጣይ ዘመናዊ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎችን ለመገንባት እንደሚሠራም አብራርተዋል። መንግሥት ከመቸውም ጊዜ በላይ ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱንም አንስተዋል።
#አሚኮ_ዜና #ጤና #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕርዳር_ሐምሌ_02_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ:-ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
