🏙 🛣️ በኮሪደር ልማት ⛰️ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አንዱ አካል ተደርጎ በትኩረት እየተሠራበት ነው።

14

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን 🌍🌎 ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀንን “የአየር ንብረት ተጽዕኖን መግታት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ መልዕክት የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት አክብሯል።

የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ የአካባቢ ጥበቃ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ እና የሁሉም ኀላፊነት ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በጎርፍ፣ በበረሃማነት እና በመሠል ተግባራት እንደሚገለጽ ተናግረዋል። ይህን ችግር አስቀድሞ የመከላከል ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት ። ከአረንጓዴ ኢነርጂ ዘርፍ ጋር የተያያዙ ሰፋፊ ሥራዎችም እየተከናወኑ እንደኾነ አንስተዋል።

በኮሪደር ልማት ሥራዎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አንዱ አካል ተደርጎ በትኩረት እየተሠራበት ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በክልሉ በዘመቻ መልክ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ እንደኾነ ነው የተናገሩት።

ዜጎች ንጹሕ አካባቢ የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ይጠቀሙ ዘንድ ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በየከተሞች በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡ ቆሻሻን በአግባቡ የማስወገድ እና መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ባሕሉን ማዳበር እንዳለበትም ተመላክቷል።
የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአየር ንብረት ለውጥ አካቶ ትግበራ ዳይሬክተር አወቀ ይታይህ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ ተግባራት በቅንጅት እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጡ በምርት እና ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው የተናገሩት አቶ አወቀ በሌሎች የልማት ዘርፎች የሚከናወኑ ሥራዎች የአካባቢን እና የአየር ንብረትን ከግምት ያስገቡ እንዲኾኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከብክለት የጸዳ አካባቢን ለመገንባት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ለ92 የቤት ማኅበራት የእጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል::
Next article🌧 በጎ ታሪኮች በሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥሞሽ ውስጥ !