🌧 በጎ ታሪኮች በሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥሞሽ ውስጥ !

10

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰኔ እና ሰኞ የሚለው ሀገርኛ ብሂል በኢትዮጵያውያን ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነገር፤ አንዳንዴም የማይገጥሙ ነገሮች ሲኖሩ እንደ ምሳሌ ሲጠቀስ የምናስተውለው ነው።

የሳምንቱ የሥራ ቀን መጀመሪያ የኾነችው ሰኞ ከሰኔ ወር መግቢያ ቀን ጋር መግጠሙ የቀናት እና የዕለታት ስሌታዊ መለዋወጥ የሚፈጥሩት ገጠመኝ እንጅ ክፉ ገጠመኝ የሚፈጠርበት እንዳልኾነ ግን ብዙዎች ይስማሙበታል።

በጎ ካልኾኑ ነገሮች ጋር ከማስተሳሰር ይልቅ አገላለጹን ከሀገራችን በጎ ታሪኮች፣ ከተፈጥሮ በረከት እና ከማኅበራዊ እሴቶቻችን ጋር ማገናኘቱ ሚዛን ይደፋል።

በኢትዮጵያ የሰኔ እና የሰኞ ግጥምጥሞሽ ትልልቅ አይረሴ ታሪኮች የተፈጠሩበት ስለመኾኑ ዛሬም ተሰንደው የተቀመጡ የታሪክ መዛግብት ሕያው ምስክሮች ናቸው።

በጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ (የአጼ ምኒልክ የግል ታሪክ ጸሐፊ) የነበሩት እና “ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ” በሚል ርእስ በተጻፈው መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው መረጃ ከአይረሴ ታሪኮች መካከል 1888 ዓ.ም ላይ ሰኔ እና ሰኞ ሲገጥሙ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ጸንቶ የቆየ ታሪክ የፈጸሙበት 🇪🇹 የዓድዋ ድል የክተት አዋጅ በአጼ ምኒልክ የታወጀበት የግጥምጥሞሹ በጎ ማሳያ ቀን ነው።

ይቺ ቀን የኢትዮጵያዊነት ወኔ የነገሠባት፤ መደማመጥ የጎለበተባት፤ አንድነት የጠነከረባት እና ዛሬ ላይ በኩራት አንገታችን ቀና አድርገን ታሪክን በዓለም ዓደባባይ እንድንናገር የሚያስችል ምዕራፍ የተከፈተባት ቀን ናት። በሰኔ እና ሰኞ ቀን አዋጁን ያስነገሩበት መልካም የድል ቀን ነው ማለት ይቻላል።

የሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥሞሽ ታሪክ በዚህ አላበቃም። በ1900 ዓ.ም አጼ ምኒልክ ወደ ኢትዮጵያ መኪና እንዲገባ ካደረጉ በኋላ በሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥሞሽ ዕለት ነጋሪት እየተጎሰመ ከ100 ዓመት በላይ የተሻገረው እና ዛሬ ላይም ጥቅም ላይ ያለው ተሽከርካሪ በቀኝ በኩል እግረኛ በግራ በኩል እንዲጓዝ አዋጅ እንዲነገር ያደረጉበትም በጎ ታሪክ ኾኖ ይወሳል።

አዋጁ “አንተ የሀገሬ ሕዝብ ሆይ ነገ ጠዋት ከመኝታህ ተነስተህ ባለ ጉዳይም ወደ ጉዳይህ ስትሔድ፤ ከብትም ያለህ ለስምሪት ስትነዳ፤ ሴቶችም ወደ ውኃ መቅጃ ስትሔዱም ኾነ ስትመለሱ ግራ መስመራችሁን ይዛችሁ ሒዱ !” የሚል ነበር፡፡

ይህ አዋጅ ለሀገሬው ሰው ግን ድንጋጤ ፈጥሮ ነበር። ንጉሱ ምን ነካቸው? ያስባለም ጭምር። ኢትዮጵያውያን በባሕል እና በልማድ የቀኝ መንገዱን የሰው መውደዱን ስጠኝ እያሉ ኑረዋልና በበጎ ከመገንዘብ ይልቅ ይህን ልማድ የሚያስቀይር መሰላቸው። ይህን ተከትሎም ሰኔ እና ሰኞ የተገጣጠሙበት 1990 ዓ.ም ቀኑን ሙሉ ጸጥ ረጭ ብሎ ዋለ ይላል ታሪኩ፡፡ ቀኑም ጥሩ አጋጣሚ ያልተፈጠረበት ኾኖ ተሳለ። ለዛሬም እርሾ ጣለ።

በወቅቱ እንግዳ እና መጥፎ አጋጣሚ ተደርጎ የተሳለው ይህ በጎ አዋጅ ጸንቶ እና ዘመን ተሻግሮ ዛሬም ሕግ ኾኖ ቢቀጥልም እንኳ 118 ዓመት ተቆጦሮ ዛሬም ድረስ የእግረኛ መንገድን ይዞ የመሄድ ባሕሉ ግን ውስንነት የሚታይበት ነው።

ተግባር ከዘመን ጋር ተራምዶ ውጤት እንዲያመጣ ማድረግ ግን ከሁሉም የሚጠበቅ ነው።

ለማሳያነት ጥቂት የሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥሞሽ የፈጠሯቸውን በጎ ታሪኮች በዘገባችን ዳሰስን እንጂ እልፍ በጎ ታሪኮች እንዳሉ መጠቆምን እንወዳለን።

በሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article🏙 🛣️ በኮሪደር ልማት ⛰️ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አንዱ አካል ተደርጎ በትኩረት እየተሠራበት ነው።
Next articleበሀገር ውስጥ በተፈናቃዮች እና በወታደራዊ ካምፖች ልዩ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች ነገ ድምፅ ይሰጣሉ።