የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ለ92 የቤት ማኅበራት የእጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል::

16

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፍኖተ ሰላም ከተማ ለዓመታት የመልካም አሥተዳደር እንቅፋት ኾኖ የቆየውን የቤት ማኅበራት ችግር መፍትሄ ለመስጠት የተሰጠው ትኩረት ፍሬ ማፍራቱ ተመላክቷል።

የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጊዜው ደግአረገ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በነበረው የጸጥታ ችግር እና በሌሎች ምክንያቶች በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለተደራጁ ዜጎች ቦታ የማስተላለፍ ሂደቱ መጓተት አጋጥሞት መቆየቱን ተናግረዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ከ250 በላይ ሕጋዊ ማኅበራት ይገኛሉ።

የዕጣ አወጣጡ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በአሳታፊነት እና በፍትሐዊነት ያቀፈ አሠራርን የተከተለ ነው። በመጀመሪያውም ዙር 92 ማኅበራት የዕድሉ ተጠቃሚ ኾነዋል። ቀሪ ማኅበራትንም በቀጣይ ዙር ለማስተናገድ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ከነዋሪዎች እና መምህራን በተጨማሪ የመከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የማረሚያ ቤት፣ የአድማ መከላከል፣ የሕዝባዊ ፖሊስ እና የሰላም አስከባሪ አባላት የዕድሉ ተጠቃሚ ኾነዋል።

ለሀገር እና ለከተማዋ ሰላም ሲሉ ሕይወታቸውን ለከፈሉ 13 የሰላም አስከባሪ አባላት ቤተሰቦች ከተማ አሥተዳደሩ ካሳ በመክፈል የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ከአርሶ አደሮች ጋር በተደረገ ሙሉ መግባባት በአጭር ጊዜ ውስጥ 56 ሄክታር መሬት 225 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ በመፈጸም ሥራውን ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል።
ለ202 የመሬት ባለቤት ወላጆች እና ልጆቻቸው የቤት መስሪያ ቦታም ዕድል ተሰጥቷቸዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይ ዓለሙ ሂደቱ የሕግ ማስከበር ድክመቶችን፣ የተዛቡ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን፣ ያልተገቡ አሠራሮችን እና የጸጥታ ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም የተሳካ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

የማኅበረሰቡን ጥያቄ ለመፍታት እና ምቹ የመኖሪያ ሁኔታን ለመፍጠር የተጀመረው ጥረት በቀጣይም በቅንጅት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የዕድሉ ተጠቃሚ የኾኑ ዜጎችም መደሰታቸውን ተናግረዋል።

#አሚኮ_ዜና #የቤት_ማኅበር_ዕጣ_አወጣጥ #ፍኖተሰላም

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሐረሪ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ውሳኔዎች።
Next article🏙 🛣️ በኮሪደር ልማት ⛰️ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አንዱ አካል ተደርጎ በትኩረት እየተሠራበት ነው።