የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ የአካባቢውን ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

17

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ቆረጣ ሥራ ላይ ገብተው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የኾኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች አሚኮ በቦታው ተገኝቶ አነጋግሯል።

ከሥራ እድል ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ ፀሐይነሽ ፈጠነ፣ ወጣት ሰለሞን አላምነው እና ወጣት አለምነሽ ከፌ ለአሚኮ እንደተናገሩት ፋብሪካው ስኳር ወደማምረት መግባቱ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

በፋብሪካው መሥራታቸው ገንዘብ እንዲያገኙ ስላስቻላቸው በኢኪኖሚ ተጠቃሚ በመኾናቸው ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውንም እያገዙ እንደኾነ ተናግረዋል። በዚህም ደስተኞች መኾናቸውን ገልጸዋል።

የፋብሪካው ዋና ሥራ አሥኪያጅ ባይነሳኝ ዘሪሁን ፋብሪካው በሦሥት ዋና ዋና ችግሮች ሥራ አቁሞ የነበረ መኾኑን አስታውሰዋል። በተለይ የገንዘብ፣ የኀይል አቅርቦት እና የጉልበት ሠራተኞች ማነስ ከፍተኛ ችግሮች እንደነበሩም ነው የተናገሩት።

የነበረውን የገንዘብ ችግር የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በጋራ አጥንተው ብድር እንዲመቻች በማድረግ ከሞላ ጎደል ችግሩ ተፈትቷል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ። ከኀይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ የቁንዝላ የኀይል ማስተላለፊ (ትራንስፎርመር) ተጠግኖ ወደ ሥራ መግባቱ ሙሉ በሙሉ ችግሩ እንዲፈታ አስችሏል ብለዋል።

ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በ2004 ዓ.ም የመሠረተ ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው ቢጀመርም በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሂደቱ በመዘግየቱ ወደ ሥራ ሳይገባ ቆይቶ በ2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ተመርቆ ስኳር ማምረት ጀምሮ የነበረ መኾኑም ይታወሳል። ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት በሰጠው ትኩረት በፋብሪካው የነበሩ ችግሮች ተፈትተውለት በተጠናከረ መንገድ ስኳር ወደ ማምረት ገብቷል።

ዘጋቢ፦ሰለሞን ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች እነማን ናቸው?
Next article“እውነተኛ እና ዘላቂ እድገት ሊመጣ የሚችለው ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተሳሰረ ሥራ መሥራት ሲቻል ነው” አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ