
ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚገኙ እና በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የአጀንዳ ሃሳቦችን ማሰባሰቡ ይታወሳል፡፡
በዚህ የምክክር ሂደት በክልል፣ ከተማ አሥተዳደር ደረጃ፣ በፌዴራል ደረጃ እና በዲያስፖራው ማኅበረሰብ ዘንድ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በኮሚሽኑ ተደራጅተው ለመጨረሻው የአጀንዳ ቀረጻ እየተዘጋጁ ነው፡፡
👉 በአጀንዳዎች ላይ የሚመካከረው ማን ነው?
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ተሳትፎን የሚያደርጉ አካላት ኮሚሽኑ አጀንዳ ካሰባሰበባቸው ባለድርሻ አካላት የተመረጡ እና የተወከሉ ሲኾን ይህም በባለድርሻ አካላቱ እውቅና ሲከናወን ቆይቷል፡፡
በዚህ መሰረት በክልሎች፣ በከተማ አሥተዳደሮች እና በዲያስፖራው ማኅበረሰብ ዘንድ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ ወቅት በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ እነሱን ወክለው የሚመካከሩ ወኪሎቻቸውን እንዲመርጡ ተደርጓል፡፡
በሌላ በኩል በኾሚሽኑ አሠራር ሥርዓት መሠረት በክልሎች፣ በከተማ አሥተዳደሮች እና በፌዴራል ተቋማት በሚገኙ እና ወኪሎቻቸውን በአጀንዳ ማሰባሰብ ወቅት እንዲመርጡ ያልተደረጉ ባለድርሻ አካላት ወኪሎቻቸውን በደብዳቤ ወክለው ለኮሚሽኑ እንዲያሳውቁ ኮሚሽኑ ለባለድርሻ አካላቱ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡
4 ሺህ የሚጠጉ አካላት በሚሳተፉበት የሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ፦
👉 የየወረዳ የኅብረተሰብ ክፍል ወኪሎችን፤ የክልል እና የከተማ አሥተዳደር ባለድርሻ አካላት ወኪሎችን፤ የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ወኪሎችን እና የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ወኪሎችን እንደሚያካትት ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
