
ደሴ: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከሌሎች ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች ጋር በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።
ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎቹ በዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር የሚገኘውን የጎፍ ውድ ፕሮዳክትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እና አማህተም ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን ነው የጎበኙት።
የጎፍ ውድ ፕሮዳክትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በዓባይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር የሚገኙት የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ እና የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሀብት ነው። የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ በጎፍ ውድ ፕሮዳክትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የ95 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ አለው። የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደግሞ አምስት በመቶ የባለቤትነት ድርሻ እንዳለው ተገልጿል። ፋብሪካው አሁን ላይ በማሽን ተከላ ላይ ይገኛል።
እስካሁን ድረስ 349 ሚሊዮን ብር ፈሰስ እንደተደረገበት ተመላክቷል። የማሽን ተከላውን የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ እየሠራው ነው። በ2019 በጀት ዓመት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተመላክቷል። ወደ ሥራ ሲገባ ለኮንስትራክሽን እና ለፈርኒቸር ሥራ የሚውል ፕሌይ ውድ እንደሚያመርት ተገልጿል። ወደ ሥራ ሲገባ ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
አማህተም ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ኃለፉነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካ የአልሙኒዬም እና የመስታወት ምርት የሚያመርት ነው። ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገባ ከውጭ ይገባ የነበረን የአልሙኒዬም ምርት በማስቀረት የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል። አሁን ላይ የማሽን ተከላ ሥራ እየተካሄደ ነው።
ፋብሪካው ሲጠናቀቅ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርም እድል ይፈጥራል ተብሏል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
#አሚኮ_ዜና #ኮምቦልቻ #ደቡብ_ወሎ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
