
ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት” ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር “ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ከባለሃብቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ የተገኙ ባለሃብቶች የግብዓት፣ የኀይል አቅርቦት እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሟላ ጠይቀዋል። የክልሉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ክልሉ ተወዳዳሪ እንዲኾን ከተፈለገ ሰላምን ማረጋገጥ እና ለኢንዱስትሪ ማነቆ የኾኑ ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት። የማስፋፊያ ቦታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባም ገልጸዋል። የፋይናንስ ተቋማት ለባለሃብቶች የብድር አቅርቦት እንዲያመቻቹም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ባለሃብቶች የሚያነሷቸውን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ችግሮች እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ውይይቶች እየተደረጉ እና አቅጣጫዎች እየተቀመጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የፋይናንስ ተቋማት የብድር አቅርቦት እንዲያመቻቹ ውይይት መደረጉንም አንስተዋል። ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱም ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ችግሮችን እየፈታ፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ምርት እንዲጨምር ያደረገ ነው ብለዋል።
“አምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚው የልብ ምት ነው” ያሉት አስተባባሪው የልብ ምት የኾነውን ዘርፍ በቅንጅት ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት። አምራች ኢንዱስትሪው ያለበትን ማነቆ እየፈቱ መሄድ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የኀይል አቅርቦትን እና ሌሎች ችግሮችን መፍታት አለብን ነው ያሉት። ከተቋማት ጋር ያለን ቅንጅት ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። ለኢንዱስትሪ የሚመጥን የሰው ኀይል መገንባት እንደሚገባም አመላክተዋል። ባለሃብቶች ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲያመርቱም አስገንዝበዋል። በተገቢው መንገድ በመሥራት ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲያላቅቁ እና በሁሉም መስክ ራሷን የቻለች እንድትኾን እንዲተጉም አሳስበዋል።
#አሚኮ_ዜና #ኢትዮጵያ_ታምርት #ደቡብ_ወሎ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
