“በምንም ኹኔታ ውስጥ ኾነን ሁልጊዜም ማምረት አለብን” አቶ መላኩ አለበል

4

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት” ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር “ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ከባለሀብቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ባለፉት ዓመታት ላለመሥራት ምክንያቶች ነበሩ፤ ነገር ግን ከምክንያት በላይ በመኾን በመሥራት ውጤት መጥቷል ነው ያሉት።

በምንም ሁኔታ ውስጥ ኾነን ሁልጊዜም ማምረት አለብን ብለዋል። ለባለሃብቶች የፋይናንስ አቅርቦት ችግር አሁንም አለ ያሉት ሚኒስትሩ ችግሩን ለመፍታት ባንኮች የማበደር አቅማቸውን ማሳደግ፤ አገልግሎታቸውን ማዘመን አለባቸው፤ ባለሃብቶች ደግሞ በአግባቡ ብድርን መመለስ አለባቸው ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ የሚሰጥ እና የገበያ ትስስር እንዲኖር እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ያለውን የኀይል አቅርቦት ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። የኢንዱስትሪ ሃብቶችን በአግባቡ ማሥተዳደር እና የኢንዱስትሪ ባሕልን መገንባት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪ ጥራት እና ውድድር ይፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ ኢንዱስትሪውን በብቁ የሰው ኀይል መምራት እና ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ችግሮቻቸውን በየጊዜው እየፈቱ መሄድ እንደሚገባም ተናግረዋል። መሬት የወሰዱ ባለሃብቶችም ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸው ገልጸዋል። መሬት ወስዶ አለማልማት ማለት ክልሉን እና ኢንዱስትሪውን መበደል ነው ብለዋል።

እያለሙ ያሉ ባለሃብቶችም ሌሎች ፕሮጄክቶችን እንዲያስቡ አስገንዝበዋል። ሰላም እና ልማት የማይነጣጠሉ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ልማት እንዲያድግ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

#አሚኮ_ዜና #ኮምቦልቻ #ደቡብ_ወሎ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት በየትኛውም ዘርፍ ማምረት ያስፈልጋል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“አምራች ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ የልብ ምት ነው ” አሕመዲን ሙሐመድ ( ዶ.ር)