“የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት በየትኛውም ዘርፍ ማምረት ያስፈልጋል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

5

 

ደሴ: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት” ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር “ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ከባለሃብቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ኢንዱስትሪዎች የሚያነሱትን የኀይል አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል። አሁንም ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራ ነው ያመላከቱት።

በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የኀይል አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል። የነዳጅ አቅርቦት ቅድሚያ ለሚሰጠው መስጠት እና ለአልሚ እንዱስትሪዎች መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር ከባንኮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጉንም ገልጸዋል። ለኢንዱስትሪ ማስፋፊያ የሚጠየቁ የመሬት ጥያቄዎችን በፍጥነት ለመመለስ እንሠራለን ነው ያሉት። ነገር ግን መሬት ወስደው አጥረው ያስቀመጡ አሉ፤ እነዚህ ወደ ሥራ መግባት አለባቸው ብለዋል።

ባለሃብቶች የወሰዱትን መሬት በጊዜው ተጠቅመውበት ቢኾን ኖሮ የክልሉ ኢንዱስትሪ ምርት አሁን ካለበት በላቀ ደረጃ ያድግ እንደነበር አንስተዋል።

የገበያ ትስስር እንዲኖር ለሀገር ውስጥ ምርቶች ቅድሚያ የሚሰጥ የንግድ መመሪያ መጽደቁንም ገልጸዋል። ኢንዱስትሪውን የሚመራ ብቁ የሰው ኀይል መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል። ባለሃብቶች በፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች አማካኝነት ብቁ የሰው ኀይል ማሠልጠን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በብቁ የሰው ኀይል ያልተመራ ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ አይኾንም ነው ያሉት። የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ማምረት ያስፈልጋል ብለዋል። የእኛ የማደግ ማዕከላዊ ሃሳብ በየትኛውም ዘርፍ ማምረት የሚል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ፤ መሪዎች ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።

አሁን የተጣለብንን ታሪካዊ ኀላፊነት ካልተወጣን ታሪካዊ ተጠያቂነት ይመጣል ብለዋል። የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ቀዳሚ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመርሐ ግብር ማሟያ አይደለም፤ ችግሮችን እየፈቱ የሚጨበጥ ሥራ መሥራት ነው ዋናው ጉዳይ ነው ያሉት።

ክልሉ ትልቅ የመልማት ጸጋ ያለው ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ለሀገር ትልቅ አበርክቶ ያለው ክልል መኾኑን ገልጸዋል። ያለውን ጸጋ በአግባቡ ማውጣት እና መጠቀም ያስፈልገናልም ነው ያሉት።

ባለሃብቶች በወሰዱት መሬት ላይ በአግባቡ እንዲያለሙ ወደ ልማት ያልገቡትም ወደ ልማት እንዲገቡ አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

#አሚኮ_ዜና #ኢትዮጵያ_ታምርት #ደቡብ_ወሎ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleያለ አምራች እንዱስትሪዎች መስፋፋት ኢኮኖሚን ማሳደግ አይቻልም።
Next article“በምንም ኹኔታ ውስጥ ኾነን ሁልጊዜም ማምረት አለብን” አቶ መላኩ አለበል