ያለ አምራች እንዱስትሪዎች መስፋፋት ኢኮኖሚን ማሳደግ አይቻልም።

8

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት” ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር “ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድአሚን የሱፍ ኢትዮጵያ ታምርት የሀገር ውስጥ ምርትን የሚያበረታታ እና የኢኮኖሚ ነጻነትን የሚያረጋግጥ መኾኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ማጠቃለያ መርሐ ግብር በከተማዋ እንዲካሄድ ስላደረጋችሁ እናመሰግናለን ነው ያሉት። ኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪ ከተማ መኾኗን ገልጸዋል።

ኮምቦልቻ ከተማ ለወደብ እና ለማዕከላዊ ገበያ የተመቸች መኾኗንም አንስተዋል። የኢንዱስትሪ እና የሎጀስቲክስ ማዕከል ኾና እንድትቀጥል በትኩረት እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።

በከተማዋ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውንም ከንቲባው ገልጸዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት የሚተኩ፤ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ እና ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ክልሉ የበርካታ ጸጋዎች ባለቤት መኾኑን ተናግረዋል። ጸጋዎችን ማልማት እና መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል። ያለ አምራች እንዱስትሪዎች መስፋፋት ኢኮኖሚን ማሳደግ እንደማይቻልም ገልጸዋል።

ሀገራት ያደጉት ለአምራች ኢንዱስትሪ በሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ነው ብለዋል። ባለፉት ዓመታት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በተሰጠው ትኩረት የአምራች ኢንዱስትሪዎች ተስፋፍተዋል፤ የማምረት አቅማቸው አድጓል፤ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ መጥተዋል ነው ያሉት።

በክልሉ ያለውን ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ መኾኑን ነው ያመላከቱት። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለሀብቶች እና መንግሥት የበለጠ እንዲቀራረቡ ያደረገ መኾኑንም አንስተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢንዱስትሪ ምርቶች የአማራ ክልል ያለፉት ዓመታት የስኬት እና የምርታማነት ማሳያ ናቸው” አቶ መላኩ አለበል