
ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት” ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር “ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ እና የምርት ከተማ መኾኗን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኢትዮጵያ ታምርት የማጠቃለያ ኤክስፖ የጽናት እና የማምረት ተምሳሌት መኾኑን አንስተዋል። ሁሉም አይነት ምርቶች በክልሉ ተመርተዋል ነው ያሉት።
በጽናት ሠርታችሁ ያገኛችሁት ውጤት ስለኾነ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል። ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገባውን የሚያስቀሩ፤ ለውጭ ገበያም የሚቀርቡ መኾናቸውን ተናግረዋል። ለበርካታ ወገኖችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ነው የተናገሩት።
ምርቶቹ የአማራ ክልል ያለፉት ዓመታት የስኬት እና የምርታማነት ማሳያ መኾናቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሃሳብ የተጠነሰሰው በደሴ ከተማ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በሰሜኑ ጦርነት የወደመውን ኢንዱስትሪ መልሶ ለመገንባት የተጀመረ እንደኾነ አስታውሰዋል።
በጦርነቱ በርካታ ሃብቶች ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል፤ ነገር ግን በችግር አንቆምም ብለን በመሥራታችን ከዚህ ደርሰናል ነው ያሉት። አሁን የተገኘው ውጤት ከችግር በኋላ ድል እንዳለ የሚያመላክት መኾኑን ገልጸዋል።
ኮምቦልቻ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል መኾኗን ነው የተናገሩት። እድገቷ በዚህ የማያበቃ እና ሰፊ እንደኾነ የተናገሩት ሚኒስትሩ ከዚህ በላይ መሬት ማዘጋጀት እና ባለሀብቶችን መሳብ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። አማራ ክልልን ባለው ጸጋ ልክ በማልማት በሀገር አቀፍ ደረጃ አስተዋጽኦን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሰላምን በመጠበቅ በአንድነት ክልሉን አና ሀገሪቱን ማልማት እና ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
