“ተወዳዳሪ እና ቀዳሚ ለመኾን በቅንጅት እና በትብብር መሥራት አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

7

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት” ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር “ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ መልዕክት በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በራስ የመኩራት፤ በራስ አቅም የማደግ፣ የራስ ምርትን የማሳደግ፣ የራስ ምርትን የመጠቀም እና በአንድ ላይ ሀገርን የማበልጸግ እሳቤ የወለደው መኾኑን ገልጸዋል።

ሀገር የተሟላ ሉዓላዊነት እና ነጻነት የሚኖራት በሁሉም መስክ ራስን መቻል ሲቻል ነው ብለዋል። እኛ በቀኝ ግዛት ያልተገዛን ሀገር እና ሕዝብ ነን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በላባችን ራሳችንን መቻል አለብን ነው ያሉት። ሕዝባችንን በድህነት እና በኋላቀርነት ከሚጠራበት ስሙ ማላቀቅ ያስፈልጋልም ብለዋል።

በምርት ራሱን ያልቻለ ሀገር የሌሎች ሀገራት ጥገኛ መኾኑ አይቀርም፤ ጥገኝነቱ ደግሞ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በማኅበራዊ ዘርፍ ይኾናል ነው ያሉት።
የሌሎች ሀገራት ጥገኛ የኾነ ሀገር ደግሞ የተሟላ ሉዓላዊነት እና ነጻነት አይኖረውም ብለዋል። የተሟላ ነጻነት እና ሉዓላዊነት እንዲኖር በምርት ራስን መቻል የውዴታ ሳይኾን ግዴታ መኾኑን ገልጸዋል።

“የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረ መምጣቱንም ተናግረዋል። በንቅናቄው ለኢንዱስትሪ የነበረው አስተሳሰብ መቀየሩንም ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ታምርት” ከተጀመረ ወዲህ የኢንዱስትሪዎች ፈተና የነበረው የኀይል እና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲሁም ሌሎች ችግሮች እየተፈቱ እንዲሄዱ እያደረገ ነው ብለዋል። የአምራች ዘርፉ በለውጥ ታሪክ ውስጥ መኾኑንም አንስተዋል።

አሁንም ለአነስተኛ፣ ለመካከለኛ እና ለከፍተኛ
ኢንዱስትሪዎች ዕድገት በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የምርት አቅም አጠቃቀም በፊት ከነበረው በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል። የክልላችን የአማራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የማምረት አቅምም አድጓል ነው ያሉት። ነገር ግን አሁንም ብዙ መሥራት ይጠብቀናል ብለዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪ በጸጥታ ችግር ውስጥ ቆይቷል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋት የጸጥታ ችግሩንም ይፈታዋል ብለዋል። ኢኮኖሚው ያደገ ሀገር እና ሕዝብ ወደ ግጭት እንደማይገባም ተናግረዋል።

በክልሉ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ትኩረት ከተደረገባቸው ዘርፎች አንደኛው የአምራች ኢንዱስትሪው መኾኑን አንስተዋል። ይህን ዘርፍ በልዩ ትኩረት መደገፍ እና ችግሮቹን እየፈቱ የተሻለ ዕድገት እንዲኖረው ማድረግ የክልሉን ኢኮኖሚ በዘላቂነት መለወጥ እና አስተማማኝ ኢኮኖሚ የመገንባት ጉዳይ ነው ብለዋል።

በሀገራት መካከል ለውጥ የሚፈጥረው በኢንዱስትሪ ዕድገት መኾኑን ነው የተናገሩት። ክልሉንም ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ማስገባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልላችን የኢንቨስትመንት አቅም እና የመልማት ጸጋን እየለየን መሥራት አስፈላጊ ብቻ ሳይኾን ግዴታ ነው ብለዋል። ክልሉ ከፍተኛ የኾነ የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት አቅም አለው፤ ይሄን አቅም አስተሳስሮ እና አቀናጅቶ መጠቀም ደግሞ ከመንግሥት እና ከባለሃብቶች ይጠበቃል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እስካሁን ያልታየውን የክልላችን ጸጋ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንድናስተዋውቅ፣ አዳዲስ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ እንዲመጡ፣ ባለሃብቶች ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው፤ ችግሮቻቸው እንዲፈቱላቸው፤ ከመንግሥት ጋር ያላቸው ቅርርብ እንዲሻሻል አይነተኛ ሚና ተወጥቷል ነው ያሉት።

ይህን ቅንጅት ማሳደግ እና አምራች ኢንዱስትሪው የበለጠ እንዲሰፋ ማድረግ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መኾኑንም አመላክተዋል።

የክልሉ ባለሃብቶች በክልሉ በስፋት እንዲያለሙም ጥሪ አቅርበዋል። የጸጥታ ችግር ሳይበግራቸው በክልሉ ለሠሩ እና ለውጤት የበቁ ባለሃብቶችን አመሥግነዋል። ሌሎችም ወደ ሥራ እንዲገቡ አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥት ባለሃብቶችን እንደሚደግፍም አስታውቀዋል።

ክልላችን ወደኋላ እንዲቀር አንፈልግም፤ መፍቀድም የለብንም፤ ክልሉ ተወዳዳሪ እና ቀዳሚ እንዲኾን በቅንጅት እና በትብብር መሥራት አለብን ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ በመልዕክታቸው።

#አሚኮ #ኢትዮጵያ_ታምርት #ደቡብ_ወሎ #አማራ #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብርን አስጀመሩ።
Next article“የኢንዱስትሪ ምርቶች የአማራ ክልል ያለፉት ዓመታት የስኬት እና የምርታማነት ማሳያ ናቸው” አቶ መላኩ አለበል