
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ሥብሠባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ሰባት ኤርፖርቶች መገንባታቸውን እና በርካታ ግድቦች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። በቅርቡም የሚጠናቀቁ ግድቦች መኖራቸውን አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ብቻ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ተሠርቷል። በሀገሪቱ አሁን ላይ ያለው የመንገድ ሥራ ፍላጎት 2 ትሪሊየን ብር ይፈልጋል ነው ያሉት።
በርካታ የመንገድ ሥራዎች በተሳኩበት ልክ ከፕሮጀክቱ በላይ በካሳ ለመጠቀም በሚደረግ ጥረት፣ የፋይናንስ ምንጭ ሳይታወቅ እና ብር ሳይያዝ ፕሮጀክቶችን በመጀመር እና በሌሎች ምክንያቶች የሚጓተቱ መንገዶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ የተጀመሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በመለየት እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
በጀትን ቆጣቢ መኾን እንደሚገባ፤ ክልሎች ገቢ ማመጨት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው፤ ሥራን በትጋት እና በሥነ ምግባር መምራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በግል ተቋም በሥራ ላይ የሚሠማሩ ድርጅቶች እንደ ነጋዴ ሳይኾን እንደ ሀገር ገንቢ ማሰብ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ተገኘ ብሎ ከመዝረፍ ይልቅ ጥራት ያለው ሥራ በማከናወን ለትውልድ የሚተላለፍ ተግባርን ሊከውኑ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለክልል የሚበጀትን በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል። በቀጣይ በጀት ዓመት በርካታ ሥራ ይጠበቅብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጤታማነት መትጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
#አሚኮ_ዜና#የሕዝብ_ተወካዮች_ምክር_ቤት_ስብሰባ#አማራ_ክልል_ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕርዳር_ሰኔ30_2018_ዓ_ም
በያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
