
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ሥብሠባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በምላሻቸውም የኢትዮጵያ እዳ አመጣጡም ግዝፈቱም ችግር አለበት ብለን ያሳለፍናቸው ውሳኔዎች የተከበረው ምክር ቤት በከፍተኛ አክብሮት ሊያየው የሚገባ ነው ብለዋል።
ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ኮመርሻል ሎን ተበድረው ደመወዝ እንደሚከፍሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ስምንት ዓመታት አንድ ዶላር ኮመርሻል ሎን አለመበደራችን ቀላል አይደለም ነው ያሉት።
ከሁለት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ እዳ መክፈል አቅቷት በሚል የተነሳው የዩሮ ቦንድ ጉዳይ ኢትዮጵያ መክፈል አቅቷት ሳይኾን እነዚያ እዳዎች በድርድር አግባብ መልክ መያዝ አለባቸው የሚል እምነት ስለነበረ ነው ብለዋል።
አበዳሪዎችን ያመሠገኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳክቶልን የዮሮ ቦንድን ጨምሮ ከብዙ አበዳሪዎቻችን ጋር ተስማምተናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የነበረባት እዳ ከአጠቃላይ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ሲነጻጸር ከ50 በመቶ በላይ ደርሶ ቀይ መስመር ውስጥ ገብታ ስለነበረ ተጨማሪ ብድር ብትወስድ ለመክፈል ትቸገራለች የሚል ነበር ክርክሩ ብለዋል።
በተሠራው ሪፎርም በአፍሪካ ውስጥ ገዙፍ ኢኮኖሚ ገንብተው አረንጓዴ መስመር ከገባ ኢኮኖሚ ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ መኾኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ባቡር ለኮመርሽያል ሎን ማሳያ እንደሚኾንም ጠቅሰዋል። እስከ ጅቡቲ የተዘረጋው ባቡር ሳያልቅ እና ሥራ በቅጡ ሳይጀምር አበዳሪዎች ብር አምጡ ማለታቸውን በማስታወስ ኮንሴሽናል ሎን ቢኾን እንደዚያ አይኾንም ነበር ሲሉ አብራርተዋል።
የእዳ ሽግሽግ ማድረግ መቻሉ ትልቅ ድል የተገኘበት መኾኑን አንስተዋል።
ላለፉት ስምንት ዓመታት አንድ ዶላር ኮመርሻል ሎን አልወሰድንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገር ውስጥ ብድር ግን አለ ብለዋል። ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ብድር ለኢንቨስትመንት እና ለልማት አስፈላጊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመክፈል የሚያስችል ቁመና መፈጠሩን ግን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
ትላልቆቹ ሀገራት ብዙ እዳ አለባቸው ሲባል እዳ መጥፎ ቢኾን ከእነሱ እንማር ነበር ነው ያሉት። እኛ በእነሱ ልክ የማንበደረው በዚያ ልክ ፕሮጀክት ሠርተን ውጤታማ ኾነን እዳችን መክፈል ማረጋገጥ ችግር ስለኾነ ነው ብለዋል።
#አሚኮ_ዜና #የምክር_ቤት_ውሎ #PMAbiyAhmed #Parliament 🇪🇹
#ባሕር_ዳር_ሰኔ_30_2018_ዓ_ም
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
