“በተጨባጭ መረጃ ተደግፎ የመጣን የሌብነት ሥራ መንግሥት አይታገስም።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር)

3

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር አቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በመንግሥት የሚመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ሌብነትን መጠየፍ ይገባል ብለዋል።

ሌብነት ጥዩፍ እና ቆሻሻ ነገር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሌብነት ከማንሳት ባለፈ በተጨባጭ መረጃ ተደግፎ የመጣን የሌብነት ሥራ መንግሥት እንደማይታገስ አስታውቀዋል።

ሌቦችን ለይቶ በሕግ እና በአሥተዳደራዊ መንገድ እርምጃ ለመውሰድ ተጨባጭ መረጃ እና ማሥረጃ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። ተጨባጭ መረጃ ለመንግሥት በማንኛውም መንገድ ቢቀርብ እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ መኾኑንም አረጋግጠዋል።

ሌብነት መጥፎ መኾኑን በመገንዘብ ተጨባጭ ማስረጃ በመያዝ መንግሥትን በማገዝ በኩል ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።

በመጭው ጊዜ ለኢትዮጵያ ሲባል ሆደ ሰፊ መኾን እና መተባበር እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት። ኾደ ሰፊ በመኾን በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን ለመፍታት፣ በውጭ ያሉትን በይቅርታ ለማስገባት፣ በጫካ ላሉት ይቅርታ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግም አመላክተዋል።

በመጨረሻም ባለፉት አምሥት ዓመታት በምክር ቤት አባልነት ቆይታቸው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ መጎልበት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና ሀገራቸውን ላገለገሉት የምክር ቤት አባላት ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

#አሚኮ_ዜና #የምክር_ቤት_ውሎ #PMAbiyAhmed #Parliament 🇪🇹

#ባሕር_ዳር_ሰኔ_30_2018_ዓ_ም

በአሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኑሮ ውድነት ጫናን ለመግታት እና የመኖሪያ ቤቶችን ለማስፋፋት የተነደፉ አዳዲስ የመንግሥት ስልቶች
Next article“ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት አንድ ዶላር ኮመርሻል ሎን አልተበደረችም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)