የኑሮ ውድነት ጫናን ለመግታት እና የመኖሪያ ቤቶችን ለማስፋፋት የተነደፉ አዳዲስ የመንግሥት ስልቶች

9

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የዋጋ ንረትን እና የኑሮ ውድነትን ለመፍታት መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን አስመልክተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት በቅርበት የተሳሰሩ ቢኾኑም ለይቶ ማየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ባለ 10 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ የዋጋ ንረትን ዜሮ ማድረስ እንደማይቻል ገልጸዋል። ጤናማ ኢኮኖሚ ከዕድገቱ ጋር ተመጣጣኝ የኾነ ባለ ነጠላ አሃዝ የዋጋ ንረትን ሊሸከም እንደሚችልም ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ያለው ዋናው ፈተና የዋጋ ንረቱ ብቻ ሳይኾን ከሕዝቡ የገቢ መጠን ጋር ባለመመጣጠን የመግዛት አቅምን የፈተነው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት መኾኑን ጠቁመዋል።

ይህንን የኢኮኖሚ ጫና ለማቃለልም መንግሥት የተለያዩ የጣልቃ ገብነት እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።

ዋጋን ለማረጋጋት፦
👉ከ2 ሺህ በላይ የእሁድ ገበያዎችን የማማደራጀት እና ምርታማነትን የመጨመር ሥራዎች ተከናውነዋል።
👉 በየወሩ የ36 ቢሊዮን ብር የነዳጅ ድጎማ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

የዋጋ ንረት ምክንያቶች፦
ከዓለም አቀፍ ግጭቶች እና ቀውሶች ጋር ተያይዞ የነዳጅ እና የማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ የምግብ እና ምግብ ነክ ባልኾኑ ሸቀጦች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ በማሳደር የውጭ የዋጋ ንረት ማስከተሉን ጠቅሰዋል።

አሁን ካለው የኢኮኖሚ እውነታ ጋር ለማጣጣም በተለይም በግሉ ዘርፍ ዝቅተኛውን የደሞዝ ወለል ማስተካከል አስቸኳይ ፍላጎት መኾኑን አንስተዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም ሕገ-ወጥ እና መደበኛ ያልኾነውን የገበያ ሥርዓት በሕጋዊ ማዕቀፎች መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ፦
👉 በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቤቶች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።
👉በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ታቅዷል ነው ያሉት።

ይህ ሰፊ የግንባታ ሥራ የሚከናወነው በመንግሥት፣ በግል ዘርፉ እንዲሁም በመንግሥት እና በግል አጋርነት አማካኝነት ነው ብለዋል።

ለዚህ ተግባር የሚረዳ ፖሊሲ ተቀርጾ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀ ሲኾን የ3D ግንባታ ቴክኖሎጂን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮችም እየገቡ ይገኛሉ ብለዋል።

ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲኾኑ ለማስቻልም አዲስ የሞርጌጅ (የቤት ብድር) ሥርዓት እየተዘረጋ ነው። በዚህም ሰዎች በቀጥታ ቤት መግዛት ካልቻሉ በኪራይ የሚጠቀሙበት ወይም ከገቢያቸው ላይ እያቆጠቡ እና እየከፈሉ በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ የቤት ባለቤት መኾን የሚችሉበት አሠራር ተመቻችቷል ነው ያሉት።

#ኢትዮጵያ #የሕዝብ_ተወካዮች_ምክር_ቤት #ዐቢይ_አሕመድ #የኑሮ_ውድነት #የዋጋ_ንረት #የነዳጅ_ድጎማ #የቤት_ግንባታ #የሞርጌጅ_ሥርዓት #ኢኮኖሚ #አሚኮ
#ባሕርዳር_ሰኔ30_2018_ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኢኮኖሚ ሪፎርሙ የሚጨበጥ ለውጥ አምጥቷል።
Next article“በተጨባጭ መረጃ ተደግፎ የመጣን የሌብነት ሥራ መንግሥት አይታገስም።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር)