የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የሚጨበጥ ለውጥ አምጥቷል።

2

 

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ሥብሠባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት አካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በኢትዮጵያ በሁሉም የልማት ዘርፎች ባለፉት ዓመታት ያልታየ ፈጣን እና ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።

አየር መንገድ አቅም በሦሥት እጥፍ አድጓል፤ በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ በረራዎች ብቻ ከ21 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን ማጓጓዝ ችሏል ብለዋል። የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም በንግድ እና በትራንስፖርት ዘርፎች የተመዘገቡት ስኬቶች የሀገሪቱን አቅም ያሳደጉ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት 17 ዓመታት የቡና ኤክስፖርት ያስገኘው ገቢ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ቢኾንም በዘንድሮው ዓመት ብቻ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ አንደኛ፣ በዓለም ደግሞ ሦሥተኛ የቡና አቅራቢ ሀገር አድርጓታል ነው ያሉት።

ባለፉት 27 ዓመታት ከወርቅ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነበር። በዘንድሮው ዓመት ግን በተወሰዱ እርምጃዎች 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ተመዝግቧል ነው ያሉት።

መንግሥት ባለፉት 27 ዓመታት ሠብሥቦት የነበረው ጠቅላላ ገቢ 1 ትሪሊዮን ብር ነበር። ዘንድሮ ግን ከ1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠብሥቧል ነው ያሉት።

​በአገልግሎት ዘርፉም 9 ነጥብ 8በመቶ ዕድገት ይጠበቃል ብለዋል። ይህ በሀገሪቱ ብቻ ሳይኾን በአፍሪካም ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል። የዘንድሮው የሸቀጦች ኤክስፖርትም ከዕቅድ በላይ 11 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አንስተዋል።

​ይህ ስኬት የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድል መኾኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። በተለይም መኪና ወደ ሀገር ውስጥ በሚያስገቡ እና በንግድ ዘርፍ ላይ በተሰማሩ አካላት ዘንድ ከሕጋዊ አሠራር ውጭ የሚደረጉ ግብይቶች እንዲቆሙ አሳስበዋል።

በአጠቃላይ ለውጡ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ውጤት ነው ብለዋል። ለውጡም “ከቁጥር በላይ የሚታይ፣ የሚዳሰስ እና የሚጨበጥ ለውጥ አስመዝግበናል፤ በቀጣይም ይህንን ስኬት በማስቀጠል የላቀ ውጤት ለማምጣት በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

#አሚኮ_ዜና #የምክር_ቤት_ውሎ #PMAbiyAhmed #Parliament 🇪🇹

#ባሕር_ዳር_ሰኔ_30_2018_ዓ_ም

በሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች።
Next articleየኑሮ ውድነት ጫናን ለመግታት እና የመኖሪያ ቤቶችን ለማስፋፋት የተነደፉ አዳዲስ የመንግሥት ስልቶች