🏙 ኮሪደር ልማት ከከተማ ውበት በላይ የሥራ ባሕልን በእጅጉ እየቀየረ ነው ።

16

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በከተሞች 🛣️ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከከተማ ውበት እና ገጽታ ባለፈ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ ያለ ትልቅ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።

ይህ ልማት ቀደም ሲል በከተሞች ይስተዋል የነበረውን የመሠረተ ልማት ቅንጅት ማጣት ችግር በከፍተኛ ደረጃ እየቀረፈም ይገኛል።

አሁን ባለው አሠራር የመንገድ፣ የውኃ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መስመሮች በአንድ ማዕቀፍ ስር በተቀናጀ መልኩ እንዲዘረጉ ዕድል ሰጥቷል። በአንዱ ተሠርቶ በሌላው የሚፈርስበትን የሀብት ብክነት አስቀርቷል። ይህም የመሠረተ ልማት ዘላቂነትን እያረጋገጠ ያለ ተግባር ነው ማለት ይቻላል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሰረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ተሻገር አዳሙ የኮሪደር ልማቱ ከ32 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል ።

የባሕር ዳርን ገጽታ በማሳደግ የጎብኝዎችን ቀልብ በከፍተኛ ሁኔታ መሳብ ተችሏልም ነው ያሉት ። በተለይም ልማቱን ከተፈጥሯዊው የጣና ሐይቅ ጋር በማስተሳሰር በርካታ መዝናኛዎች እና መናፈሻዎች በመከፈታቸው ለነዋሪዎች እና ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል። ይህም የከተማዋን የኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳደገው ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ሱሌማን እሸቱ የኾሪደር ልማቱ በክልል ደረጃ 🧑‍🔧👷‍♂️ ከ120 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል። ልማቱ ሥራን በጥራት እና በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚቻል አሳይቷልም ነው ያሉት።

በአብዛኛዎቹ ከተሞች እስከ ምሽት ድረስ የመሥራት ልምድ በመዳበሩ አዲስ እና ጠንካራ የሥራ ባሕል እንዲጎለብት አድርጓል ብለዋል።

ቀደም ሲል አንዱ ሲገነባ ሌላው የሚያፈርስበት ልማድ ተቀይሮ የቴሌ፣ የመብራት፣ የውኃ እና ሌሎች የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት የቅንጅት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ መፈታቱን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ክረምት ከመግባቱ በፊት ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ሥራዎቹ ተከፋፍለው ሌት ከቀን ርብርብ እየተደረገባቸው እንደኾነ ነው የተናገሩት።

የኮሪደር ልማት ከተማን የማስዋብ ሥራ ብቻ ሳይኾን የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽል እና የሀገርን የኮንስትራክሽን ዘርፍ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኮምቦልቻ ከተማ 145 ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ታምርት ክልላዊ የማጠቃለያ መድረክ ዛሬ ይካሄዳል።
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብርን አስጀመሩ።