
ደሴ: ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል “ኢትዮጵያ ታምርት” ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ነገ በኮምቦልቻ ከተማ ይካሄዳል። የማጠቃለያ መርሐ ግብሩ “ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ መልዕክት ነው የሚካሄደው።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተፈሪ ታረቀኝ ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የነበሩ ችግሮችን እየፈታ መምጣቱን ገልጸዋል።
የማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ከመካሄዱ አስቀድሞ 159 የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄዎች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ማምረት አለባት ያሉት ምክትል ኀላፊው ማምረት የሕልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መኾኑን ነው የገለጹት። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአማራ ክልል በርካታ ትሩፋት እያመጣ ነው ብለዋል።
ንቅናቄው የክልሉን ጸጋዎች በማስተዋወቅ አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ እንዲመጡ ማድረጉን ተናግረዋል። ባለፉት ወራት 414 ቢሊዮን ብር ሀብት ያስመዘገቡ 3 ሺህ 518 ባለሀብቶች ወደ ክልሉ መጥተው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማውጣታቸውን አስታውቀዋል።
880 ባለሀብቶች ደግሞ ፕሮጄክቶችን አቅርበው ማስገምገማቸውን ገልጸዋል። 158 መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ ወደ ምርት መግባታቸውንም አንስተዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ አምራች እንዱስትሪው እንዲያድግ እያደረገ መኾኑን ነው የገለጹት።
በክልላዊ ማጠቃለያ መርሐ ግብሩ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኤክስፖ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራቾች ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ፤ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ እና ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በማጠቃለያ ኤክስፖው 145 ኢንዱስትሪዎች እንደሚሳተፉም አንስተዋል።
በመርሐ ግብሩ በባለፉት ዓመታት ውጤታማ ለነበሩ አምራች ባለሀብቶች ዕውቅና እንደሚሰጥም አመላክተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ኤክስፖው እየገቡ ምርቶችን እንዲጎበኙ እና በኤክስፖው ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
