“ሚሊሻ የሰላም ምንጭ እና የሕግ መከታ ነው”

13

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን የማጠቃለያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር አካሂዷል።

የክልሉ ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ የሚሊሻ ኃይል ሕዝባዊ ሚሊሻ ተብሎ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የውጭ እና የውስጥ ጠላትን በመመከት ከፍተኛ ሀገራዊ ገድል መፈጸሙን ተናግረዋል።

የአሁኑ የአማራ ክልል ሚሊሻም ላለፉት ዓመታት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመኾን የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ግንባር ቀደም መስዋዕትነት ከፍሏል ብለዋል። “ሚሊሻ የሰላም ምንጭ እና የሕግ መከታ እንደኾነም” ገልጸዋል።

አሁንም የውስጥ እና የውጭ ጽንፈኛ ኃይሎች በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ የከፈቱትን ጦርነት ለመመከት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል ነው ያሉት።

በቀጣይ ሀገራዊ እና ክልላዊ የቤት ሥራዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት ሀገር በመኾኗ ከአጎራባች ሀገራት ጋር በሰላም የመኖር እና አብሮ የማደግ ጥያቄ እንዳላት ጠቁመዋል። መላው ሕዝብ እና የሚሊሻ አባላት በቅንጅት በመሥራት የአካባቢያቸውን ሰላም ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

ሕዝቡ ለሠራዊቱ የሚያደርገው ድጋፍ የራሱን ሰላም እና ሕይወት በባለቤትነት የመጠበቅ ጉዳይ እንደኾነም አንስተዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) በዓሉ የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ሥራ ይበልጥ ለማጠናከር፣ ዝግጁነትን ለማደስ እና ለክልሉ ዘላቂ ሰላም በጋራ ለመቆም አዲስ ቃል የሚገባበት ነው ብለዋል።

የአማራ ሚሊሻ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሀገር ድንበር ጠባቂ፤ የሕዝብ ደኅንነት አሥከባሪ እና በችግር ጊዜ ፈጣን ምላሽ ሰጭ በመኾን ማገልገሉን ተናግረዋል።

ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሀገራዊ ሉዓላዊነት እና በክልላዊ የጸጥታ ፈተናዎች ወቅት የማይረሳ የታሪክ አሻራ ማሳረፉንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት የሰላም ጥሪዎችን እና የሕግ ማስከበር ሥራዎችን እያስቀጠለ ይገኛል ነው ያሉት። የሕዝብን ሰላም፣ ሕይወት እና ንብረት አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን ለመከላከል መንግሥት ባለው ቁርጠኛ አቋም ውስጥ የሚሊሻው ሚና ከፍተኛ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሚሊሻ ለሕዝብ እና ለሀገር የሚኖር ሁነኛ የሰላም እና የልማት ዘብ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ተግባራት የአካባቢ ጥበቃን እና ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ጋር አጣምረው የያዙ ናቸው።