“ሚሊሻ ለሕዝብ እና ለሀገር የሚኖር ሁነኛ የሰላም እና የልማት ዘብ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

9

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን 30ኛ ዓመት የምሥረታ ቀን ማጠቃለያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ፤ ሚሊሻ ከሕዝብ አብራክ የወጣ፤ ከሕዝብ ጋር የሚኖር እና ለሕዝብም የቆመ ሁነኛ የሰላም ዘብ ነው ብለዋል።

ሚሊሻ ከትንሿ መንደር እስከ ታላቋ ሀገር ድረስ ሰላምን የሚጠብቅ፣ ራሱን ለሰላም እና ለልማት የሰጠ ኃይል ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ሚሊሻ ደመወዙን የኢትዮጵያ ክብር፤ ሽልማቱን የሕዝብ ሰላም ያደረገ ሀገር እና ሕዝብን አስቀዳሚ ክቡር አገልጋይ ነውም ብለዋል።

ሰላም ሲኾን ያለማል፤ ሀገር ተደፈረች በተባለ ጊዜ ደግሞ የግል ምቾቱን ወደጎን በመተው በራሱ ትጥቅ እና ስንቅ በመውጣት ቀድሞ ደራሽ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ሚሊሻ ለኢትዮጵያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና አንድነት መጽናት በደማቁ የተጻፈ ታሪክ ያለው ኃይል ስለመኾኑም አንስተዋል።

የሚሊሻ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ሲዘከር የሚሊሻ አገልግሎት ከዛሬ ሰላሳ ዓመት ወዲህ ነው ማለት አይደለም፤ ይልቁንም በክልሉ መደበኛ መዋቅር እና አሠራር ተዘርግቶለት የተቋቋመበትን ጊዜ ለመዘከር ነው ብለዋል። የሚሊሻ የአገልግሎት ጊዜ ግን ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ እና የሀገርን ክብር ከትውልድ ትውልድ ያስተላለፈ ነው ብለዋል።

የክልሉ የሚሊሻ ኀይል በቅርብ ጊዜያትም የክልሉን ሕዝብ እና የሀገርን ሰላም የሚያውኩ ላኪ እና ተላላኪዎችን በመመከት ለሰላም መስፈን ሲሠራ መቆየቱን ርእሰ መሥተዳድሩ አንስተዋል። አሁንም ቢኾን የሕዝብን ሰላም ለማወክ የሚጥሩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጠላቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። የሚሊሻ ኃይሉ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ እና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋርም በትብብር በመሥራት የሕዝብ ሰላም ዋስትናነቱን አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም አሳስበዋል።

የክልሉ መንግሥት ለሕዝብ ሰላም የቆሙ የሚሊሻ አባላትን እንደሚደግፍ አረጋግጠው፣ ሕዝቡም የሰላሙ ዘብ ለኾኑት የሚሊሻ አባላት ተገቢ ክብርና እንክብካቤ መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

#አሚኮ_ዜና #ሰላም_ማስከበር_አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሚሊሻ የሕዝብ የሰላም ዋስትና ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article“ሚሊሻ የሰላም ምንጭ እና የሕግ መከታ ነው”