“ሚሊሻ የሕዝብ የሰላም ዋስትና ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

11

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን የሚሊሻ 30ኛ ዓመት የምሥረታ ቀን ማጠቃለያ መርሐ ግብሩን በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ እንደ ሀገር ተወስኖ፣ ታቅዶ እና በትጋት ተሠርቶ ምርጫ ተካሂዷል ብለዋል። ይህ ምርጫ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የአማራ ክልል ሚሊሻ ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመኾን ታሪክ የሚያስታውሰው አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸው ምሥጋናም አቅርበዋል።

ሚሊሻ ትልቅ ሕዝባዊ የሰላም ዘብ ነው፤ በጽናት ቆመው የሀገርን ሰላም እና ልማት የሚጠብቁ የሚሊሻ አባላት ክብር እና ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ሚሊሻ ትክሻውን እና ክንዱን እንደ አስፈላጊነቱ የሚጠቀም ብርቱ የሕዝብ ልጅ ነው፤ ማኅበረሰብ ጸጥታው ሲናጋ እና ሀገር ፈተና ውስጥ ስትኾን በክንዱ ሰላምን ያስከብራል፤ ሰላምን አስፍኖም ትክሻውን ለሰላም እና ለሀገር ዕድገት ያውላል ብለዋል።

ወቅቱ የሀገር እና የሕዝብን ሰላም ለማወክ እና ልማትን ለማስተጓጎል የሚቋምጡ ባዕዳዎች እና ተልዕኳቸውን ተሸካሚ ባንዳዎች የበዙበት መኾኑን በውል መገንዘብ እንደሚገባም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

የሚሊሻ አባላት የሕዝብን ሰላም በንቃት መጠበቅ እና ሕዝቡም ለሚሊሻ አባላቱ እና ቤተሰቦቻቸው አስፈላጊውን ክብር እና እንክብካቤ ማድረግ ይገባዋልም ነው ያሉት።

የሚሊሻ አባላት ሰላምን ከማስጠበቅ በተጨማሪ የሕዝብን አንድነት ለመሸርሸር የሚነዙ የሀሰት ትርክቶች እና ወሬዎችን መመከት፤ የሰላም ዋስትና መኾን አለባቸው ነው ያሉት።

“ሚሊሻ የሕዝብ የሰላም ዋስትና ነው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የሰላም ኀይል የበለጠ እንዲዘምን እና የአባላቱ ኑሮም እንዲሻሻል እንደሀገር በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

#አሚኮ_ዜና #ሰላም_ማስከበር_አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

ዘጋቢ፦አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሚሊሻ የቁርጥ ቀን የሕሊና ወታደር ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article“ሚሊሻ ለሕዝብ እና ለሀገር የሚኖር ሁነኛ የሰላም እና የልማት ዘብ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ