“ሚሊሻ የቁርጥ ቀን የሕሊና ወታደር ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

9

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባሕርዳር በተካሄደው የአማራ ክልል ሚሊሻ 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ሚሊሻ የሀገር እና የሕዝብ ጥሪ ሲመጣ ማረሻውን ከቀዬው አኑሮ፣ መሣሪያውን በትከሻው አድርጎ ወደ ግንባር የሚተም የቁርጥ ቀን የሕሊና ወታደር ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ሚሊሻ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ከፌደራልና ከክልል የፀጥታ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት፣ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የሕዝብን ሰላም ለማስከበር ታላቅ መሥዋዕትነት የከፈለ ሕዝባዊ ኃይል መኾኑን ገልጸዋል።

ይህ ኃይል ልዩ የሚያደርገው ካለበት ማኅበረሰብ የወጣ፣ አብሮ የሚያርስና የሚያመርት፣ ሀገርና ክልል በገጠሟቸው ፈተናዎች ሁሉ ግንባር ቀደም በመኾን መሥዋዕትነትን በመክፈል ለሀገር ትልቅ አስተዋጽዖን አበርክቷል ነው ያሉት።

ሀገራችን እና ክልላችን ከተለዋዋጭ እና ውስብስብ የፀጥታ ተግዳሮቶች ጋር እየተጋፈጡ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ተቋማዊ አቅምን መገንባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።

መንግሥታችን የሚሊሻውን ኃይል አደረጃጀት ዘመናዊ ለማድረግ፣ በዕውቀት እና በሥልጠና ለማበልጸግ፣ በቴክኖሎጂ ለማዘመን፣ ትጥቅና አቅርቦቱን ለማሻሻል የጀመረውን ተቋማዊ የሪፎርም ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ሲሉ ሕይወታቸውን ለሰጡ ጀግኖቻችን ታላቅ አክብሮትና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ምርጫውን ለማደናቀፍ የውጭ ባዳዎች እና የውስጥ ባንዳዎች ያደረጉት ዕቅድ ከሽፏል” የሰላም ሚኒስትር ሙሐመድ እድሪስ
Next article“ሚሊሻ የሕዝብ የሰላም ዋስትና ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ