
አዲስ አበባ፡ ግንቦት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም ሚኒስትር ሙሐመድ እድሪስ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው እንዳብራሩት ለውጡን የማይፈልጉ አካላት ሀገራችን እንዳትረጋጋ ዘመናዊ ቴክኖሎጅን እና ሚዲያን በመጠቀም የተለያዩ አፍራሽ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
የመንግሥትን ሥልጣን በኀይል ለመንጠቅ የሚፈልጉ ኀይሎች የውጭ ባዳዎችን ተልዕኮ ተቀብለው አፍራሽ ድርጊቶችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አብራርተዋል። በቅርቡ የተካሄደውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ለማደናቀፍም አለን በሚሉት አማራጮች ሁሉ ሞክረው አልተሳካላቸውም ብለዋል።
ሕዝቡን “ምርጫ ካርድ እንዳታወጡ፣ በምርጫ ድጋፍ እንዳትሳተፉ፣ እንዳትመርጡ” የሚል የተለያዩ የማስፈራሪያ ፕሮፖጋንዳዎችን ሲነዙ መቆየታቸውን አንስተዋል። ሕዝቡ ግን ሁሉንም ጥሪዎች ባለመቀበል አሸንፏቸዋል ነው ያሉት።
ሕዝቡ ሀገርን የሚያስቀጥል ቅቡልነት ያለው መንግሥት ያስፈልገኛል በሚል ጽኑ ዕምነት ካርድ ከማውጣት ጀምሮ ድምጹን እስከመስጠት ድረስ ቁርጠኝነቱን ማሳየቱን ገልጸዋል።
ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሚፈልገውን መርጧልም ነው ያሉት። በዚህም “ምርጫውን ለማደናቀፍ ያደረጉት የውጭ ባዳዎች እና የውስጥ ባንዳዎች ዕቅድ ከሽፏል” ብለዋል።
ምርጫውን ለማደናቀፍ ሞክረው አልሳካላቸው ያሉት እነዚህ ኀይሎች የሽብር ድርጊቶችንም ጭምር መሞከራቸውን ጠቁመዋል። በሸኔ የሽብር ቡድን በኦሮምያ ክልል አርሲ ዞን አስኮ ወረዳ የተፈጸመው የሽብር ድርጊትም ለዚህ በማሳያነት አንስተዋል።
ይህም ኾነ ብለው የኅብረተሰቡን አብሮነት ለመሸርሸር ያለመ ስለመኾኑም አንስተዋል። ድርጊቱ አሳዛኝ መኾኑን ገልጸው በጽኑ የሚወገዝ ነው ብለዋል። ሁሉም ሊያወግዘው እንደሚገባም ተናግረዋል።
ግጭቱ ሲከሰት ነዋሪዎችን ለመጠበቅ እና ድርጊቱን ለመከላከል ሲታገሉ የመንግሥት የጸጥታ ኀይሎችም መስዋትነት ከፍለዋል ነው ያሉት።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች የሚተላለፉ መረጃዎች ኀላፊነትን በመውሰድ፣ አብሮነትን እና አንድነትን በማይሸረሽር መልኩ መኾን እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።
የሰላም ሚኒስቴር ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለማርገብ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን አብራርተዋል። መንግሥት ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በቀጣይም የእነዚህን ኀይሎች ሴራ በመበጣጠስ አብሮነታችንን በማጎልበት ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
