
ዛሬ የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱን ተርሚናል መርቀናል። ለኢትዮጵያ ቁልፍ የበረራ በሮች አንዱ ለሆነው ለዚህ አውሮፕላን ማረፊያ ትልቅ ምዕራፍ ነው። ይህ ፕሮጀክት ከዘመናዊ ተርሚናል በላይ ትርጉም አለው።
ባህር ዳር በቅርብ ጊዜያት ካስተናገደቻቸው ፈተናዎች ማግስት፤ የዚህ ተርሚናል ግንባታ ተጠናቆ አገልግልት መጀመር የፅናት፣ የማገገም እና ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ማረጋገጫ ነው።
አዲሱ ተርሚናል ሰፊ የአውሮፕላን ማቆሚያዎችን፣ የላቁ መሰረተ ልማቶችን፣ የተስተካከሉ መዳረሻ መንገዶችን እና ዘመናዊ መገልገያዎችን ያካተተ ነው።
ይህም የአውሮፕላን ማረፊያውን የመቀበል አቅም በማሳደግ የአካባቢውን እያደገ የመጣ ፍላጎት የሚያሟላ ሲሆን፣ ለመንገደኞችም ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ይሰጣል።
ይህ አዲስ ተርሚናል ከተማዋን እያደሰ ካለው የከተማ ትራንስፎርሜሽን ጋር ተዳምሮ፤ ባህር ዳርን ለዓለም አቀፍ እና ለሀገር ውስጥ በረራዎች ሌላኛዋ ቁልፍ መዳረሻና ማዕከል ያደርጋታል። ባህር ዳርን የመሰለች ንቁ ከተማ የምታስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላሙን መጠበቁን እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ።
