ሕዝቡ ሰላም ውድ ስጦታ መኾኑን ተገንዝቦ በጋራ እንዲቆም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አሳሰቡ።

14
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ ተርሚናልን ሲመርቁ ባስተላለፉት መልእክት፤ ሀገራዊ የልማት ስኬቶችን አስጠብቆ ለማስቀጠል የከተማዋን የገቢ አቅም ማሳደግ እና አስተማማኝ ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ መኾናቸውን በአጽንኦት አሳስበዋል።
ምንም እንኳን ባሕር ዳር ከተማ እንደ አዲሱ አየር ማረፊያ፣ ግዙፉ የዓባይ ድልድይ፣ ዘመናዊ ሪዞርቶች እና ስታዲየምን የመሳሰሉ ትላልቅ መሰረተ-ልማቶችን ብትገነባም በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያላት የገቢ ማመንጨት ደረጃ ሰባተኛ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
የተሠሩትን ፕሮጀክቶች ለመጠገን፣ ለመንከባከብ እና ተጨማሪ ልማቶችን ለማምጣት ከተማዋ የገቢ አቅሟን ማሳደግ እንዳለባት ገልጸዋል።
ለዚህም መላው ነዋሪ፣ የክልሉ መንግሥት እና የከተማዋ አሥተዳደር በመቀናጀት ባሕር ዳርን ለቱሪስቶች እና ለባለሀብቶች እጅግ ምቹ በማድረግ የሚገባትን ገቢ እንድታመነጭ በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ልማትን ለማስቀጠል ሁለተኛው አና ቁልፉ ጉዳይ ሰላም መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳባቸውን ለማስረገጥ በባሕር ዳር ከተማ በደግነታቸው ይታወቁ የነበሩትን የአቶ አሕመድ ወሎን (አባ ኑሩ) ታሪክ በምሳሌነት አንስተዋል።
ታሪኩ አንደኛው ልጇ ሠርቶ ሲያመጣ ሌላኛው ልጇ ሰርቆ የሚያባክንባት እናት ብሶትን የሚያሳይ ሲኾን “ቀኙ የሠራውን ግራ እያፈረሰው..
“አልቅሶ ከመኖር ዕድሜ ዘመኑን አይቆነጥጥም ወይ ቀኙ ግራውን” በሚለው የአባ ኑሩ ግጥም ታጅቦ ቀርቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ታሪክ በማንሳት አፍራሽ የኾኑ ኅይሎችን ማስቆም ካልተቻለ የተጀመሩ የልማት ተስፋዎች ሊበላሹ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
አዲሱ አየር ማረፊያ ራሱ የቀድሞው ተርሚናል በግጭት ሲመታ ችግሩን ወደ ዕድል በመቀየር ለትውልድ የሚሻገር ኾኖ እየተገነባ መኾኑንም አስታውሰዋል።
ባሕር ዳር ከበርካታ የአፍሪካ ዋና ከተሞች የላቀ አቅም እንዳላት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መላው ሕዝብ ሰላም ውድ ስጦታ መኾኑን ተገንዝቦ በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳ በሠለጠነ መንገድ በንግግር በመፍታት ጊዜ ሳያልፍ በጋራ ለልማት መተባበር እንደሚገባም አሳስበዋል።
✍️ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article**የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልእክት፦**
Next articleበሙስናና ሕገ-ወጥ አሠራር የተሳተፉ አካላት ላይ የሕግ እርምጃ ተወሰደ።