
ሃብት ትርጉም የሚኖረው ለተቸገሩ ወገኖች ሲተርፍ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሕር ዳር ዲስትሪክት ዳይሬክተር ደሞዜ ባልቢ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ85 ዓመታት ጉዞው ከአገልግሎት ባሻገር ለሀገር ልማት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ባንኩ ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ለማኅበራዊ ኀላፊነቶች ማዋሉን ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአዲሱ ዓመት በሁሉም ዲስትሪክቶች 72 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ከ6 ሺህ 600 በላይ ወገኖችን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ዛሬም በባሕር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 240 ወገኖች 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወጭ የኾነበት የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደርጓል። የስንዴ ዱቄት፣ ዘይት እና 2 ሺህ ብር ነው ድጋፍ የተደረገው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ባንኩ ማዕድ ከማጋራት በተጨማሪ ሴቶች እና ወጣቶች በገንዘብ እጥረት ምክንያት ከሥራ ውጭ እንዳይኾኑ ብድር በመስጠት ከተረጂነት ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ እየሠራ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ከዕለታዊ ፍጆታ እና እርዳታ በዘለለ ወጣቶች ቋሚ ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባንኩ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በመወጣት በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላደረገው የማዕድ የማጋራት ምሥጋና አቅርበዋል።
ሃብት ትርጉም የሚኖረው ለተቸገሩ ወገኖች ሲተርፍ እና ለበጎነት ሲውል በመኾኑ ሌሎች ተቋማት እና ግለሰቦችም በዚህ በጎ አድራጎት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባሕል ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል። በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የታየው በጎ ጅምር ዓመቱን በሙሉ ተጠብቆ እንዲሄድም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የበዓል መዋያ ድጋፉ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ ትልቅ ስንቅ እንደሚኾናቸው ድጋፍ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።
በዕለቱም ከማዕድ ማጋራቱ ጎን ለጎን የኅብር ቀንን በማስመልከት የደም ልገሳ፣ የጽዳት፣ የጤና ምርመራ እና የስፖርት እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል።
#አሚኮ #አዲስዓመት #ድጋፍ #አሚኮ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_04_2018_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
