‎🤝🎨 የጋራ እሴቶች፣ የጋራ ሀገር 🇪🇹

1

‎
‎የኅብር ቀን ሲነሳ ትውስታችን ወደ ጥልቅ ታሪካዊ ትስስራችን እና የጋራ እሴቶቻችን ይጓዛል።
‎
‎ቀኑ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ቋንቋ፣ ባሕል እና ታሪክ ባለቤቶች ቢኾኑም በአብሮነት፣ በእኩልነት እና በመከባበር ላይ የተመሠረቱ መኾናቸው ጎልቶ የሚቀነቀንበት ነው። ኢትዮጵያውያን በልዩ ልዩ ቀለሞች ቢታወቁም እንኳ የአንድነት ገመድ ደግሞ መለያቸው ነው።
‎
‎ኅብረ ብሔራዊነት ዜጎች ያለ ማንም ከፍታ እና ዝቅታ፣ በዜግነታቸው ዕኩል ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሚያስችል የፍትሕ ማዕቀፍም ነው። የኅብር ቀን ይህንን ውብ ኅብረ ብሔራዊነት በማክበር ለጋራ ሰላም እና ልማት ቃል የሚታደስበት አጋጣሚም ነው።
‎
‎በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህር እና ተመራማሪው መስፍን ፈቃዴ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊነት በአንድ ቀን የተፈጠረ ወይም የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ውቅር ሳይኾን የረጅም ዘመናት ታሪካዊ ሂደቶች በሕዝቦች እንቅስቃሴ እና ማኅበራዊ ትስስር እንዳይፈታ ተደርጎ የተገመደ ነው ብለዋል።
‎
‎ይህ ታሪካዊ የሕዝቦች መጋመድ እና ውሕደት ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በሚደረግ የሕዝብ እንቅስቃሴ እና የንግድ እንቅስቃሴ ሕዝቦች ተዋልደዋል፣ ተጋብተዋል ነው ያሉት። ይህም ፍጹም የኾነ የብሔር ወሰን መስመርን ወይም ድንበርን ማስቀመጥ እንደማይቻል ያሳያል ብለዋል።
‎
‎ባሕላዊ ተቋማት እና የጋራ እሴቶች መገንባታቸው፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ፈጥረዋል ነው ያሉት። እንደ ዓድዋ ጦርነት ያሉ ታሪካዊ ክስተቶች የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም እና በብሔር ሳይከፋፈሉ በአንድነት የቆሙባቸው ሁነቶች እና ሕያው ማሳያዎች ናቸው ይላሉ።
‎
‎የቋንቋ፣ የምግብ፣ የሙዚቃ እና የሥነ ልቦና ብዝኀነት አንዱ ከሌላው ጋር ተዋሕዶ በጋራ እንዲኖር ያስቻሉ መገለጫዎች መኾናቸውንም አንስተዋል። የደጋ እና የቆላ ሕዝቦች የተፈጥሮ እና የኢኮኖሚ ትስስርም የማይበጠስ ሀገራዊ ኅብረትን ፈጥሯል ብለዋል።
‎
‎ባሕላዊ የእርቅ መፍቻ መንገዶቻችን እና የሀገር በቀል ዕውቀቶቻችን ለዛሬው ማኅበራዊ ሰላም ማረጋገጫዎች መኾናቸውንም ነው የገለጹት።
‎
‎ዘመን ተሻግረው ሊያግባቡን የሚችሉ እሴቶችን በመጠቀም መጪውን ጊዜ የተስፋ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም መክረዋል።
‎
‎#አሚኮ #ኅብር #ኢትዮጵያ 🇪🇹
‎
‎#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_04_2018_ዓ_ም
‎
‎✍️ በሥራውድንቅ ደሳለው
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleማዕድ ማጋራት፦ ከምግብ ባሻገር ፍቅር እና ክብር
Next articleሃብት ትርጉም የሚኖረው ለተቸገሩ ወገኖች ሲተርፍ ነው።